Logo
Getu Temesgen
የሕዳሴው ግድብ ተስፋዎች
#ethiopia | የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሚከተሉት አራት ነጥቦች ላይ ተስፋ ይዞ የመጣል ብዬ አስባለሁ። እነዚህም ሳይንሳዊ እሳቤ፥ ራስን መቻል፥ የጋራ ተጠቃሚነት እና በተፋሰስ አገሮች መተማመን ናቸው። በአጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

1. ሳይንሳዊ እሳቤ

‘Nullius in verba’ ይላል በ1660ዎቹ የተቋቋመው የሮያል ማሕበር መርሕ/moto/ ። ይህ ሀረግ ከላቲን ቋንቋ የመጣ ሲሆን ‘ሰው የሚነግርህን ምንም ጉዳይ ላይ ቢሆን ሳትሞክር አትስማ፤ አትውሰድ ወይም አትቀብል’ የሚል ትርጓሜ ይሰጣል። ይህም የአውሮፓ የህዳሴ ዘመን መመሪያ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

የሕዳሴ ግድብ ሥራን ገና ከጅምሩ ለማየት እድሉን ካገኙ ሰዎች አንዱ ነኝ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከተወጣጣ አንድ ቡድን ጋር የሕዳሴ ግድቡን የሥራ ሁኔታ ለመገምገምና ለመማር በተደጋጋሚ ጉብኝት አድርጌያለሁ። ስለዚህ ከመስማት ባለፈ ካለኝ ልምድ ጥቂት ማለት እችላለሁ:: በቀዳሚው ጉብኝቴ አንድ የማይረሳኝ ገጠመኝ አለኝ:: በሚያዚያ ወር መጀመሪያ 2006ዓ.ም. ላይ ባድረግነው ጉብኝት የሥራውን ሁኔታ ከጉባ ተራራ ላይ ሆነን የግድቡን ግንባታ ቁልቁል ተመለከትን። ከሩቅ ሆኖ ሲያዩት የግድቡ ሥራ በጣም ትንሽ ይመስል ነበር። ከዚያም በቅርበት የሥራውን ሁኔታ እንመልከት ብለን የግድቡ ሥር ደረስን። ይህን ግዜ ግድቡ ሳይሆን እኔ ትንሽ እንደሆንኩ ተሰማኝ።

ልክ እንደዚሁ የሕዳሴ ግድብ ትልቅነትና ስፋት ብዙ ነገርን ያሳንሳል። አሁን ለምሳሌ ግድቡን ለመስራት ጥቅም ላይ የዋለው የኮንክሪት መጠን 10ሚልዮን ሜትሪክ ቶን አካባቢ ይገመታል። በቀጥታ ለማወዳደር ቢያስቸግርም እስከዛሬ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የኮንደሚኒየም ግንባታ የወሰደውን የኮንክሪት መጠን እጥፍ ሊሆን ይችላል። ከሚይዘው የውሃ መጠን አንፃር የህዳሴ ግድብ 74 ቢልዮን ሜትር ኩብ ውሃ ያጠራቅማል። አንድ ሰው ለመጠጥ በአማካኝ በቀን እስከ አምስት ሌትር ቢጠቀም ይህ ውሃ የዓለምን ሕዝብ ለአምስት ዓመታት ቀጥ አርጎ ሊይዝ ይችላል። ውሃው የማይሠርግ፣ የማይፈስ፣ እና የማይተን ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከ ሦስት መቶ ዓመት ድርስ የመጠጥ ውሃ ፍጆታ ሊሸፍን ይችላል። ውሃ የሚተኛበትን የቆዳ ስፋት ብንመለከት ከ1800 ካሬ ኪሎሜትር በላይ ይሆናል። ይህም ማለት የአዲስ አበባ ከተማን የቆዳ ስፋት ከሦስት እጥፍ በላይ ያክላል። የእኔዋ መዘዞ ወይም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የልጅነት ስፍራ የሆነችው በሻሻ እንደ ብዙዎቹ አነስተኛ ከተሞች ስፋታቸው አንድ ካሬ ኪሎሜትር እንኳ አይሞላም። ይህ ማለት የሕዳሴው ግድብ የሚያርፍበት ቦታ ሁለት ሽህ በሻሻን ወይም ሁለት ሽህ መዘዞን የሚያክል ቦታ ይይዛል ማለት ነው።

የግድቡን ሥራ ‘በርቀት ስመለከተው ያነስብኝ’ እና ‘ስቀርበው ያሳነሰኝን’ ጉዳይ ሳስብ እንኳንስ ያላዩትን ነገር ቀርቶ በዓይን የተመለከቱትንም ቢሆን መጀመሪያ የቆሙበትን ቦታ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ከበዙ ስተት ሊያተርፍ ይችላል። ይህም የሰሙትንም ሆነ ያዩትን ነገር እንዳለ ከመውሰድና ከመቀበል ለሳይንሳዊ ልኬት ቅድሚያ መስጠት ይበልጥ ከእውነታው ያቀራርባል የሚለውን ትምህርቴን በተግባር እንዳረጋግጥ ረድቶኛል።

የሕዳሴው ግድብ መገባደድ የሳይንሳዊ ልኬት እና የሳይንሳዊ እሳቤ ወጤት ነው። ሳይንሳዊ እሳቤ እንደዚህ ጨዋታ ቀያሪ ለውጥ ያመጣል። የግድቡ ዳር መድረስ በራሱ የሳይንሳዊ እሳቤ እንዲስፋፋ ሰፊ በር ይከፍታል የሚል እምነት አለኝ። ይህም የሕዳሴ ግድብን እንደስሙ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ዘመን ፈር ቀዳጅ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

2. እራስን መቻል

ዓባይ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነበር። በተመዘገበው ታሪካችን ከዛሬ 800 ዓመት ጀምሮ ዓባይን የመገደብ ፍላጎት እንደነበር ይጠቀሳል። እንደ ዐፄ ይስሐቅ ያሉት ነገስታት ከአውሮፓ ባለሞያዎች ለማስመጣት እና ለማሰራት ማሰባቸው ይወሳል። ሆኖም ንጉሱ ሀሳባቸውን እውን ላለማድረጋቸው ሁለት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው ምክንያት የራስ የሆነ ባለሞያና የቴክኖሎጂ አቅም እጥረት ነው። በውስጥና በውጭ ፋታ የማይሰጥ ጦርነት እንደ ሁለተኛ ምክንያት ይቀርባል።

ሆኖም ኢቴረም የሚባለውን የምናባዊ ገገንዘብ/cryptocurrecy/ ተቋም መስራች ከሆኑት አንዱ ቪታሊክ ቡተሪን ‘The most important scares resources is legitimacy’ በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ እንዳስቀመጠው በህዝብ ትብብር የሚሰራ ሥራ ትልቁ ጉዳይ ሕዝቡ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ሕጋዊነት እና ባለቤትነት ጋር ይያያዛል። የሕዝብ መዋጮን በታማኝነት ወደ ሥራ መለወጥ ሌላ ትልቅ ጉዳይ ነው።

እንደ ዩኒቨርስቲ መምህርነቴ ለሕዳሴው ግድብ በሁለት ወር ደመወዜ ቦንድ ገዝቻለሁ። ብዙ የመንግስት ሰራተኛ እንዲዚሁ ካለው ገቢ ቦንድ ገዝቷል። የግል ዘርፉም በሕዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ሂደት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልክ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊም ተሳትፎ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከገቢ የማሰባሰብ አንጻር ሲታይ የሕዳሴው ግድብ በሕዝብ የተሰራ ሀውልት ነው ማለት ይቻላል። በሂደቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የግድቡ ባለቤት ሆኗል። በሕዳሴው ግድብ ውስጥ ሁሉም የራሱን ፊት የሚያይ ይመስለኛል::

በሌላ በኩል የግድቡ ዳር መድረስ ከሕዝቡ የተሰበሰብው ሀብት ለታቀደለት ግብ ለመዋሉ ማሳያ ሆኖ ይኖራል። የመዋጮው ማረፊያ በታላቅ ስኬት ግዘፍ ነስቶ መታየት እና የአጠቃቀሙ ብሩህ ተስፋ ግድቡን የዘመናችን በሀገር የመተማመን ዐቢይ ስራ ያደርገዋ። በዚህም የህዳሴ ግድብ ሥራ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በላይ ማህበረሰብን ትኩረት ላደረገ የፈጠራ ሥራ ትልቅ ምልክት ይሆናል። ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያ በሀሳብ፣ በእውቀት፣ በትጋት እና በአመራር ታላቅ ክዋኔ እንደሚፈፅሙ የተማመኑበት ህያው ቅርስ ሆኖ ይኖራል በዩ ተሰፋ አደርጋለሁ።

3. የጋራ ተጠቃሚነት

ፓል ሮዳን የተባለ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ‘Big push’ የሚለውን ንድፈ ሃሳብ በ1940ዎቹ ካቀረበ በኋላ ለአንድ አገር የኢንዱስትሪ እድገት ከፍተኛ የሆነ ግፊት እንደሚያስፈልግ አስቀምጧል። በተግባርም ተሞክሮ በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ በኢስያ አገሮች ውጤት አስመዝግቧል ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቋማት በተለይም በአምራች ዘርፉ ውስጥ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በአማካኝ ያላቸውን የማምረት አቅም 50 በመቶ እንኳን እንደማይጠቀሙ በተለያየ ጊዜ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህ ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ተቋማት ያለባቸውን ችግር የሚዳስስ ጥናት ውስጥ ተሳታፊ ነብርኩ። ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሆነ ለ80 በመቶው የአምራች ኢንዱስትሪው የመብራት ኃይ መቆራረጥ የምርት ሥራን የሚገታ ምክንያት ተደርጎ ይቀመጣል። ለዚህ የመብራት ኃይል አቅርቦት ውስንነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።

የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል የማምንጨት አቅም በእጥፍ ይጨምረዋል። በትንሹ የመብራት አቅርቦትና የኢንዱስትሪ እድገትን በትዩዩ ብናስቀምጥ እንኳን የአምራች ዘርፉ እስካሁን የገጠመውን ችግር በመፍታት አሁን ካልበት ከ6 በመቶ ብዙም ያልዘለለው የምርት መጠን በእጥፍ ቢያድግ የኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ ይዘት ከሳሃራ በታች ካሉ አገሮች አማካኝ ሊያልፍ ይችላል። የአምራች ዘርፍ እድገት በራሱ የሌሎች ዘርፎችን ማለትም የግናባት፥ የግብርና፥ እና የአገልግሎት ዘርፎችን እድገት በማቀጣጠል የእትዮጵያን እድገት ሊያረጋግጥ የሚችልበት እድል ይዞ ይመጣል ብዬ ትልቅ ተስፋ አለኝ።

እዚህ ላይ አንደ የቻይና ታሪክ ብጠቅስ ደስ ይለኛል። ከክርስቶስ ልደት ከአመስት መቶ ዓመት በፊት ይሆናል። በተራራ በተከበበችው በቸንዱ ከተማ አካባቢ ትልቅ ወንዝ ነበር። ይህን ወንዝ በወቅቱ የነበሩት ንጉስ መጀመሪያ ለሁለት ከፈሉት። ቀጥለውም እያንዳንዱን የተከፈለ ወንዝ መልሰው ለሁለት እየከፈሉ በሂደት የወንዙ ኃይል በመቀነሰ ውሃውን ለመሰኖ ሥራ ማዋል ችለዋል። ከተራራ ላይ ተሰብስቦ ትልቅ ኃይል የፈጠረውን ወንዝ በብልኀት በመያዝ ትልቅ የመስኖ ሥራ ፈጥረዋል። ይህ ለዘመናዊ የመስኖ ሥራ አንድ ምሳሌ ሆኖ ኖሯል። የህዳሴ ግድብም ለዘመናት አሻፈረኝ ብሎ የኖረውን የዓባይ ወንዝ የውሃውን ፍሰት ለመብራት ኃይል ማመንጫ በመጠቀም በአጠቃላይ ለምጣኔ ሀብት እድገት ከሚያበረክተው አሰተዋጽኦ በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በተለያየ መንገድ ይዳረሳል። ከዚህ አንፃር መጀመሪያ የሚጠቀሰው የኤሌትሪክ መብራት ተደራሽነት ነው። ተደራሽነቱ ገና ከ50 በመቶ ብዙም ባልተሻገረበት አገር ውስጥ ከህዳሴው ግድብ የሚመነጨው ኃይል ለኢንዱስትሪ እና ለሌሎች አገልገሎት ባይውል በኢትዮጵያ ያሉ ቤቶች ሁሉ ውስጥ በርካታ አንፖሎችን የማብራት አቅም ይፈጥራል። ልክ እንደዚሁ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሕዳሴው ግድብ የሚመነጨው የመብራት ኃይል የእህል ወፍጮ እንዲስፋፋ በማድረግ የእናቶቸን ድካም በእጅጉ ይቀንሳል።

ይህን ኃይሉን በመረዳት ይመስላል የአማርኛ መዛግብተ ቃላቶቻችን ዐባይ የሚለውን ቃል ዋና፣ ታላቅ፣ ቀዳሚ፣ አንጋፋ፣ አባት እና ከመሳሰሉት ቃላቶች ጋር አያይዘው ይተርጉሙታል:: በብዙ የሀገራችን ባህሎች ዋና፣ ታላቅ፣ ቀዳሚ፣ አንጋፋ ወይም አባት የሆነ ሁሉ ሰብሳቢ አሰባሳቢ ነው:: ዐባይም ከጥንት ከስሪቱ ከሁሉም አካባቢ ውሀ ሰብስቦ መፈጠሩ ለስሙ የመጠነ ቢያሰኘውም ውሀ ለሰጡት ኢትዮጵያውያን ጥቅም ሳይሰጥ በመፍሰሱ የአሰባሳቢነት ፀጋውን አጥቶ ቆይቷል:: ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሰሩለት ግድብ መልሶ የስሙን ፀጋ ለብሷል:: ሰብሳቢ አሰባሳቢ ዐባይ ዐባይ ሆኑዋል:: ለጋራ ተጠቃሚነት እና ኅብረት ቁሳዊም፣ ተግባራዊም፣ ትርክታዊም፣ መንፈሳዊም፣ ሥነልቦናዊም ታዛ ሆኑዋል።

4. የተፋሰሱ አገሮችን መተማመን

የዐባይ ወንዝ በዓለም ረጅሙ ወንዝ እንደመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስራ አንድ አገሮችን እንደሚያቋርጥ ይታወቃል። የተፋሰሱ አገሮች በተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ፥ በጅኦ ፖለቲካ፥ በቴክኖሎጅ እድገት ደረጃ ወይም በሌላ ምክንያት አንዱ ከአንዱ የተለያየ ቢሆንም ወንዙን ለመጠቀም ግን ሁሉም ይፈልጋል። ሆኖም ለረጅም ዘመናት የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ይበልጥ ተጠቃሚ ሆነው እንደዘለቁ ግልጽ ነው።

የሕዳሴ ግድብን ሐሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ እዚህ እስኪደረስ ኢትዮጵያ ብዙ ሂደቶችን አልፋለች። ዐፄ ኃይለሥላሴ የመነሻ ዲዛይን አሠርተው ነበር። የሚያስፈልገውን ገንዘብ ባለማግኘታቸው ወደ ግንባታ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። የሚችል ትውልድ ሲመጣ ይሠራዋል ብለው ተናግረው አለፉ። በጠ/ሚ መለስ ጊዜ ወደ ሥራ መግባት ቻለ። በለውጡ ጊዜ ደግሞ በመቆም ላይ የነበረው የግድቡ ፕሮጀክት እንደ ገና ነፍስ ዘርቶ ወደ ፍጻሜው ደርሷል። ከተጀመረ ጀምሮ ከየትኛውም የዓለም የውኃ አካል በተለይ ብዙ የውጭ ጫና ደርሷል። የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ምን ያክል ከባድ ጫና ውስጥ እንዳለፉ አንድ ማሳያ ነው።

ይህን ሁሉ ፈተና ተቋቁሞ የሕዳሴ ግድብ መገባደድ ከኢትዮጵያ አልፎ በተፋሰሱ አጠቃቀም ላይ በመጠኑም ቢሆን የለውጥ ብርሃን ፈንጥቋል። ማንም ወንዙን መጠቀም አይችልም ከሚል እሳቤ ወጥቶ ‘የኢትዮጵያ መንግስት አሳሪ ውል/binding contract/ ይግባ፤ ተፈጥሯዊ የወንዙ ውሃ ፍሰት እንዳይቀንስ መተማመኒያ/guaranty/ ይስጠን’ ወደሚሉ ጥያቄዎች ተለውጧል። እነዚህ ጥያቄዎች በራሳቸው በቀላሉ የሚታዩ ባይሆኑም የአንዱ ጥቅም ሌላውን በማይጎዳ መልኩ የጋራ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ በተፋሰሱ አገሮች መተማመንን በመፈጠር ላይ ይገኛል።

የቴክኖሎጅ ተደራሽነት ባደገበት በዚህ ዘመን የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ከውድድርና ግጭት ወጥተው ሁሉን አቀፍ የሆነ የትብብር ማዕቀፍ በመንደፍ የሁሉንም አገሮች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻልበት እድል ሰፊ ይመስለኛል።

በጥቅሉ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከላይ ባነሳኋቸው ጉዳዮች ማለትም የሳይንሳዊ እሳቤ መስፋፋት፥ ሥራዎችን መከወን የሚያስችል የራስ አቅም መዳበር፥ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና በተፋሰሱ አገሮች መካከል የሚፈጠር መተማመን ወደፊት ከሕዳሴው ግድብ የላቀ ሥራ ለመስራት ትልቅ ተስፋ ይሰጣሉ የሚል እምነት አለኝ። የተፈጠረውን መልካም እድል በሚገባ መጠቀም ደግሞ በዚህ ትውልድ እጅ ያለ አደራ ይመስለኛል።

አመሰግናለሁ!

(የህዳሴው ግድብ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የቀረበ)

ምስጋና ለNebiyou Baye
ፎቶ ከWondwossen Mulugeta

ዶክተር ብርሃኑ በሻህ እንደፃፈው

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.