Logo
YenetaTube
የአዉሮጳ ዘማቹ ቃኘዉ ክፍለጦር ሲታወስ !
‎
‎“አጨደው ከመረው ወቃው እንደ ገብስ፤
‎የኢትዮጵያ አርበኛ ኮሪያ ድረስ።”
‎
‎
‎ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት ነበር ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በመውረር የጦርነት አዋጅ ያስነገረችው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያን የጠብ ጫሪነት ተግባሯን በአስቸኳይ እንድትታመኑ ወረራዋን እንድታቆም ወደ ሰላማዊ ህይወቷ እንድትመለስ አስጠነቀቀ ሰሜን ኮሪያ አሻፈረኝ አለች ።
‎
‎የጸጥታው ምክር ቤትም ለዓለም ሰላም ሲባል ወረራው ለመቀልበስ ውሳኔውን የደገፉ አሥራ ስድስት የዓለም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ስፍራው እንዲልኩ ጥሪ አቀረበ ።ከነዚህ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ ትገኝበታለች ።
‎
‎ከአሥር መድፈኛ ሻለቆች ተውጣጥቶ 1122 መኮንኖችንና ወታደሮችን ያካተተ አዲስ “ቃኘው ሻለቃ” የተሰኘ ክፍለጦር ተቋቋመና ስምንት ወራት የፈጀ ስልጠና ሲወስድ ቆየ ።
‎ በመጨረሻም ሚያዚያ 5 ቀን 1943 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ባሉበት የቃኘው ሻለቃ አባላት ችሎታቸውን ለማሳየት ወታደራዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡
‎
‎ንጉሡም፡- “እነሆ በጋራ ደኅንነት መርሕ መሠረት፤ እጅግ ቅዱስ ለሆነው ለዓለም ሰላም ዘብ ልትቆሙ፣ የዓለምን ግማሽ የሚሆን ጉዞ ትጓዛላችሁ። ሂዱና ወራሪዎችን ድል ንሱዋቸው። በኮሪያ ልሳነ ምድርም ሕግና ሥርዓትን አስከብሩ፡፡ ይሄን ሰንደቅ ዓላማ መመሪያ አድርጋችሁ እንድትዘምቱ፣ በተሰማራችሁበት ቦታ ጀግንነት ሠርታችሁ በደረታችሁ ላይ ልዩ ምልክት አድርጋችሁ በኩራት ስትመለሱ በአደራ የሰጠናችሁን አርማ መልሳችሁ እንድታስረክቡን” በማለት ነበርሞራል ሰጥተው በክብር የሸኟቸው፡፡
‎
‎ከጀግኖች ምድር የበቀሉት 1122 የመጀመሪያው ዙር የቃኘው ሻለቃ አባላት “እልም አለ ባቡሩ እልም አለ ባቡሩ፣ ወጣቱን ይዞ በሙሉ” በሚለዉ በድምፃዊ ካሳ ተሰማ ታጅቦ በባቡር ወደ ጅቡቲ ከኋላም በመርከብ ፑዛን ወደተሰኘችው የኮሪያ የወደብ ከተማ ደረሱና ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው በሁለተኛው ዙርም ተጎዘ ሶስተኛዉም ሰለሰ በአጠቃላይ በአምስት ዙር 6037 ወታደሮች የቃኘው አባላት ኮሪያ ዘምተዋል ።
‎ታዲያ በወቅቱ አንድም ከአፍሪካ የዘመቱ ብቸኛ ወታደሮች በመሆናቸው ሁለትም ነጮች ለጥቁር በነበራቸው ንቀት ይህን ጦርነት ይቋቋማሉ ብሎ ያመነ አልነበረም አንዳንዶቹም እንዲያዉ ለአመል እንጂ የት የለመዱትን ዉጊያ ተጠቅመው ድል ሊያስመዘግቡ እያለ ተሳለቀ፡፡
‎
‎ የማይቀረው የሜዳ ላይ ዉጊያዉ ተጀመረ አለም የጠበቀዉ ቀርቶ ያላሰበዉ ሆነ የጦረኞቹ ደም በዉስጣቸዉ ያለዉ የቃኘዉ ክፍለጦር ወታደሮች ጠላትን ያርበደብዱት ገቡ ።
‎
‎በኮሪያው ዘመቻ ወቅት ዋና ዋና ውጊያዎች የሻለቃ ጦር ጀብደኝነት መታየት ጀመረ ። በሽምቅና በደፈጣ ውጊያ የሚደርስበት ታጣ የከባድ መሳሪያ ተኳሽና የሞርታር ዓላሚነትም እየመረጡ ይቀነድቡት ተያያዙ ።
‎በግግር በረዶ ሥር ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎች የሚመክኑት በቃኘው ሻለቃ አባላት ነበር ።
‎ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮችም ቃኘዉ ክፍለጦር
‎በቁጥር 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል የቆጨ ብቸኛው ጦር ሆነ ።
‎ከዘመቱት ከስድስት ሽህ በላይ ዘማቾች መካከል 122ቱ በጦርነቱ ሞተዋል። 536 ወታደሮች ቆስለዋል። የተማረከ ግን አልነበረም፡፡
‎
‎በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ ሃገር ናት፡፡ ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ ደቡብ ኮሪያ 8343፣ አሜሪካ 4714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራሊያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ 3፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ 5፣ ኔዘርላንድ 3፣ ቤልጅየም 1፣ ፊሊፒንስ 97፣ ፣ ኒውዚላንድ 1 ፣ ኖርዌይ 3 ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች።
‎የኢትዮጵያ ጀግንነት ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ይሰማ ጀመር የቃኘው ሻለቃ አባላት በጦርነት የተሰዉ አባሎቻቸውን አስከሬን ለጠላት ጥለው እንደማይሮጡ እሳት እየዘነበባቸው የጓዶቻቸውን ክቡር አስከሬን ተሸክመው ሲሮጡ የሚያሳይ ቪዲዮ ተሰራጨ።
‎
‎የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላት በኮሪያ ምድር በቆዩበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያዎች እንደ ልዩ አይቀመሴ ፍጡር ያዪቸው ነበር። እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፤ “ኢትዮጵያውያን እልኸኞች ናቸው። መማረክን አይቀበሉም። ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው፤ ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ” ሲል ለማወደስ ጽፎላቸዋል።
‎ኢትዮያ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ሰራዊቷን ወደ ጦርነቱ ከመላክ በተጨማሪ የ400 ሺ ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
‎በሐምሌ ወር 1945 ዓ.ም የኮሪያ ጦርነት ጦርነትን በማቆም ስምምነት ተጠናቀቀ።
‎
‎ከጦርነቱ በኋላም የቃኘው ሻለቃ አባላት ለሶስት ዓመታት በኮሪያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር የሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል።
‎
‎ ለመጨረሻም በመጋቢት ወር 1948 ዓ.ም የጦሩ አባላት ሙሉ ለሙሉ የኮሪያን ምድር ለቀዉ ሀገራቸው ገቡ ።
‎
‎አንደኛው ሻለቃ ለመጀመርያ ጊዜ ከጠላት ነፃ በወጣው ‹‹ቻንቹን›› ከተማ ውስጥ ለኢትዮጵያ የኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል። ይህንን ሐውልት የመረቁት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ በሐውልቱ አካባቢ ጣሪያቸው በሳር ክዳን የተሸፈኑና የኢትዮጵያን ባህላዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁ ጎጆዎች ተገንብተዋል፡፡ በጦርነቱ ከፍተኛ ተጋድሎ የፈጸሙና ድል የተቀዳጁ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለአራት የተመድ አባል አገራት መከላከያ ኃይሎች መታሰቢያ የሚሆንና በየአገሮቻቸው ስም የሚጠሩ አዳራሾችም ታንፀዋል። ከሁሉም ትልቁ አዳራሽ የኢትዮጵያ አዳራሽ ነው፡፡
‎
‎ዘማቾችን ወደር የለሽ ጀግንነት አዝማሪዎች በስንኝ አወድሰውታል፡፡
‎“አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት
‎ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት”
‎
‎ እኛም ለዛሬው ይህንን ባለታሪክ ክፍለጦር በዚህ መልኩ ልናስታውሰው ወደድን ።
‎
‎ታዴ የማመይ ልጅ
‎

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.