Logo
YenetaTube
ከታክስ ማጭበርበር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው 217 ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት ከታክስ ማጭበርበር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ 217 ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ለአሐዱ አስታውቋል።

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ በበጀት ዓመቱ ገቢ በማሰባሰብ ረገድ ጥሩ የሆነ አፈፃፀም መኖሩን ገልጸው፤ በዛው ልክ በታክስ ማጭበርበር የተጠመዱ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች እንደነበሩ አንስተዋል።

በነዚህ የተነሳ እርምጃ ከተወሰደባቸው 217 የቢሮው ሠራተኞች መካከል 12ቱ ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"እነዚህ ግለሰቦች ደንበኛን በአግባቡ ባለማስተናገድ፣ ሰዓት ባለማክበርና ከታክስ ከፍይ ጋር በመመሳጠር ታክስ ለማጭበርበር የሞከሩ ናቸው" ሲሉ አስታውቀዋል።

ቢሮው በመልካም አስተዳደር ተጠርጥረው በተገኙ ግለሰቦች ላይ እንደየ ወንጀላቸው ታይቶ የፁሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ከሥራ ማገድና እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ መወሰኑን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አስታውቀዋል።

"የትኛውም የተቋሙ ሠራተኛም ሆነ አመራር እንዲሁም ታክስ ከፋይ፤ ታክስ ለማጭበርበር ቢሞክር ከሕግ ማምለጥ እንደማይችል ማሳወቅ የተቻለበት የበጀት ዓመት ነበር" ሲሉም ተናግረዋል።

"ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ ነው" የሚሉት አቶ ሰውነት፤ ነገር ግን ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ቢሮው ከሚጠቀመው የአሰራር ስርዓት ማምለጥ እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

ነገር ግን ባሳለፍነዉ የ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመቱ ቢሮው ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተለያዩ እንቅፋቶች አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም፤ 243 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 233 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታውቋል።

ይህም 83 በመቶ አፈፃፀሙን ማሳካት መቻሉን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰውነት አያሌው ለአሐዱ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በታክስ ኦዲት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በድጋሚ ኦዲት በማድረግ፤ የውሳኔ ጥራትን የሚያረጋግጥ አዲስ የሥራ ክፍል በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

አዲሱ የኦዲት ጥራት አረጋጋጭ የሥራ ክፍል ከዚህ ቀደም በታክስ ኦዲት በሚወሰኑ ውሳኔዎች ምክንያት የሚፈጠሩ ክፍተቶች እና ብልሹ አሰራሮችን በአሰራር የሚዘጋ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ግብር ከፋዩ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ካለው በተዘረጉ ሕጋዊ አሰራሮች ብቻ በመጠቀም እንዲሁም በ7075 ነጻ የስልክ መስመር ቅሬታውን እና ማንኛውንም ጥቆማ ማቅረብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ ተመላክቷል፡፡

(አሐዱ ሬዲዮ)

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.