“ሥልጣኔዎቿ ከባሕር ጋር ይያያዛሉ፣ ታሪኮቿ ከባሕር ጋር ይተሳሠራሉ”
#ethiopia | እርሷ ባሕሩን ከየብሱ ጋር አስማምታ ገዝታለች፤ ሀገረ መንግሥትን ከዘመናት በፊት አጽንታለች፤ ሕግና ሥርዓትን አስተምራለች፡፡
ለዘመናት በረቀቀ እና በጸና ሥርዓት ኖራለች፡፡ ጥላ ላጡት ጥላና ከለላ ኾናለች፡፡ አርዓያና ምሳሌ ተደርጋ በዓለሙ ሁሉ ተጠርታለች፡፡ መንገድ ለጠፋባቸው መንገድ አሳይታለች፤ ሥልጣኔ ለራቃቸው የሥልጣኔን መስመር አስተምራለች፡፡
በጥበብ እና በሥልጣኔ ጎዳናዎች ተረማምዳለች፤ የድል አድራጊነት ሐውልቶችን አቁማለች። ከዓለሙ በተለየ ኪነ ሕንጻን አንጻለች። ነጻነትን ከዓለት አጠንክራ አጽንታለች፤ በነጻነት ላይ የመጡባትን ሁሉ ድል መትታለች፤ እርሷ በባሕር ንግድ የዓለም ዳርቻዎችን አካልላለች፡፡
በእርሷ ምድር ብቻ የሚገኙትን ዕንቁ ሀብቶች በባሕር እና በየብስ ለዓለሙ ገበያ አቅርባለች፡፡ ከዓለም ዳርቻዎች የሚመጡትን ነጋዴዎችም በወደቦቿ ተቀብላለች፡፡ በጎዳናዎቿም በሰላም እንዲመላለሱ ፈቅዳለች፡፡
በበዙት ወደቦቿ የሚወጣውን ሸኝታለች፤ የሚገባውን ተቀብላለች፡፡ በየብሱ እና በባሕሩ በገነባችው ሠራዊት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ አይነኬ ሀገርነቷን በዓለሙ ሁሉ አስመስክራለች። ሥልጣኔዎቿ ከባሕር ጋር ይያያዛሉ፡፡ ታሪኮቿ ከባሕር ጋር ይተሳሰራሉ፡፡ እርሷን ያለ ባሕር ማሰብ አይቻልም፡፡
ቀይ ባሕር ቀለሟ ነው ታሪኳን የጻፈችበት፣ ቀይ ባሕር ብራናዋ ነው ታሪኳን ያሰፈረችበት፣ ቀይ ባሕር ማንነቷ ነው ሥልጣኔዎቿን ያሳያችበት፤ ቀይ ባሕር መንገዷ ነው ወደ ከፍታ የተጓዘችበት፤ ቀይ ባሕር ድልድዩዋ ነው ከዓለማት ጋር የተገናኘችበት፣ ቀይ ባሕር ማሕተሟ ነው የታሪክ እውነታዎቿን ያተመችበት፣ ቀይ ባሕር አዋጅ ነጋሪዋ ነው ታላቅነቷን ለዓለም ሁሉ የነገረችበት፣ ቀይ ባሕር እልፍኟ ነው የውጩ እና የውስጡን ያሰባሰበችበት።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና አካባቢው ያለውን ግዛቷን ባሕረ ነጋሽ እያለች ስታስተዳድር ኖራለች። ይህም እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ድረስ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር በታሪክ እና በማንነት ባይለያዩም፣ ቀይ ባሕር ያለ ኢትዮጵያ ባይታሰብም፣ ኢትዮጵያም ያለ ቀይ ባሕር ታሪኳ ባይነገርም ለዓመታት ሃብቷን አጥታ ኖራለች። ይህም ብዙ አጉድሎባታል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ባሕረ ነጋሽ የአሁኗ ኤርትራ ሀገር ከኾነች ጀምሮ ኢትዮጵያ ታሪክ የቀመረችባቸውን፣ ሥልጣኔዋን ከፍ ከፍ ያደረገችባቸውን፣ ጥበብ እና ሃይማኖት የነገረችባቸውን፣ ወዳጆቿን የተቀበለችባቸውን ወደቦቿን አጥታ ኖራለች። ይህም ብዙ አጉድሎባታል።
የአፍሪካ አብነት፣ የጥቁሮች እመቤት የኾነችው ኢትዮጵያ ታላላቆች ልጆቿ አስከብረውት የኖሩት የታሪኳ እና የማንነቷ ውብ ቀለም ቀይ ባሕር ያስፈልጋታል። የእርሷ ነበርና ለእርሷ ይገባታል።
ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ሰው ሁሉ በተፈጥሮው እኩልነት ያለው ነው፡፡ በታሪኩ ግን ይለያያል፡፡ አንዱ ከአንዱ በልጦ ይገኛል፡፡ አንዱ ለቆመለት ከፍተኛ ዓላማ የግል ጥቅሙን መስዋዕት ለማድረግ የሚያበቃው ጀግንነት ሲኖረው ሌላው ተቃራኒው ፈለግ በመከተል ኑሮውን ይመራል፡፡
የጀግና ልቦና ለሀገሬ እንጂ ለራሴ ከሚል ግላዊ ሀሳብ የራቀ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ለሀገሬ እንጂ ለራሴ ከሚል ግላዊ እሳቤ ወጥተው ለኢትዮጵያ ኖረዋል፤ ስለ ኢትዮጵያ አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትከበርበትን እና ከፍ ከፍ የምትልበትን አድርገዋል። ሁሉንም ለሀገራቸው ሰጥተዋል፡፡ ነፍሳቸውን ሳይቀር ለኢትዮጵያ ከፍታና ልዕልና አድርገዋል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ለራሴ በሚል ግላዊ እሳቤ የነበሩ ጥቂቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ብዙ ነገር አሳጥተዋል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ቀይ ባሕርን ያጣችበት መንገድ ነው። በዚህ ዘመን ደግሞ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት እና እንደሚገባት በግልጽ የጠየቁ መሪዎች መጥተዋል። ይህም ከራስ አልፎ ለሀገር እና ለወገን ማሳብ ነው።
ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን የባሕር በር ያላት፣ ጥንታዊት ሀገር መኾኗን ጽፈዋል፡፡ እርሷ ከቀደሙ ጥንታውያን ሥልጣኔ ከነበራቸው ሀገራት በአዶሊስ እና በሌሎች ወደቦቿ አማካኝነት በመርከብ ንግድ ታሳልጥ እንደነበር እና ከሀገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ታደርግ እንደነበር መዝግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ከተመዘገበበት ዘመን ጀምሮ ቀይ ባሕር ብቻ ሳይኾን ከቀይ ባሕር ባሻገር የነበሩ ሀገራትም የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ሲነገር ኖሯል። ለዚህም ደግሞ በዓላት ላይ የተቀረጹ፣ በብራና የሰፈሩ፣ በወረቀት የተከተቡ አያሌ ማስረጃዎች ሞልተዋል። ይህ ብቻ አይደለም በሕይወት ያሉ አያሌ ሰዎችም ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር እንደማይነጣጠሉ ዛሬም በሕይወት ይመሰክራሉ።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ቡሩክ ኃይሉ ኢትዮጵያ የኋላ ታሪኳ ሲነገር፣ ሥልጣኔዋ ሲመዘዝ የዳህላክ፣ የአዶሊስ እና የሌሎች ወደቦች ባለቤት እንደነበረች፣ በባሕሯ በቀይ ባሕር አማካኝነት ከግሪክ እና ከሮማውያን ጋር ትገናኝ ነበር ነው የሚሉት፡፡
የሺህ ዘመናት ታሪኳ ሲነገር ኢትዮጵያ እና ባሕር በር አይነጣጠሉም፡፡ እርሷ አንድ ብቻ ሳይኾን በርከት ያሉ ወደቦች የነበሯት ሀገር ናት ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በባሕር ላይ ሥልጣኔዋ በታሪክ አንቱ የተባለች ናት፡፡ የቀይ ባሕር ባለቤት ብቻ ሳትኾን ከዚያም ተሻግራ ሀገራትን ታስተዳድር እንደነበር ታሪክ ይመዝዛሉ፡፡ ቀይ ባሕር ቤቷ፣ መግቢያ እና መውጫዋ ነው ይላሉ፡፡ የቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ የሚተረክ አይደለም የእርሷ ነውና፡፡
ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ነው የባሕር በር ያጣችው የሚሉት ምሁሩ አሁን ላይ የራሷ የነበረውን የባሕር በር እንደሚገባት በግልጽ ጠይቃለች፤ ጥያቄዋም ታሪካዊ፣ ሕጋዊ እና እውነትን መሠረት ያደረገ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግም እንደሚደግፋት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሀገር የባሕር በር ያስፈልጋታል፡፡ ይገባታልም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እስካኹን ድረስ መጠቀም የሚገባትን ሳትጠቀም ቆይታለች፤ በሚያሳዝን ኹኔታ የባሕር በሯን ተነጥቃ ቆይታለች ነው የሚሉት፡፡
የኢትዮጵያ አኹናዊ ቁልፍ የዲፕሎማሲ ሥራ ታላቋ፣ ታሪካዊቷ እና ጥንታዊቷ ሀገር የባሕር በር እንዲኖራት ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት፣ በዚህ መንገድ ታፍና መኖር እንደሌለባት እየተሠራ ነው፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ጥረት ታደርጋለች፤ ጥረቷን ከጎረቤቶቿ ሀገራት ጋር አጠናክራ ትቀጥላለች ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለባሕር በር የቀረበች መኾኗን ነው የተናገሩት፡፡ በርካታ ሀገራትም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ እንደኾነ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ማግኘት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እየገለጹ ነው ይላሉ፡፡
ሕዝብ እና መንግሥት ሲናበቡ ታላላቅ ሥራዎችን ይሠራሉ የሚሉት ምሁሩ የፖለቲካዊ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በሀገራዊ ጉዳይ ልዩነት ሊኖር አይገባም፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ሲኾኑ የማይሠሩት ታላቅ ሥራ የለም ነው የሚሉት፡፡ ሀገርን በማስቀደም፣ ሀገር የምትጠይቀውን በመስጠት የታሰበውን ማስፈጸም የዚህ ዘመን ትውልድ አደራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የዚህ ዘመን መንግሥት ጥያቄ ብቻ አይደለም፣ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው፤ መንግሥት በሕዝብ ተደግፎ ሲሠራ የባሕር በር ጥያቄው ይሳካል ነው የሚሉት፡፡
ወጥ እና የተባባረ ኀይል ይዘን ከቀጥልን የትኛውም ችግር ሊበግረን አይችልም ይላሉ፡፡ የባሕር በር ጥያቄ የሀገር እና የሕዝብ ጥያቄ ነው። ጥቅሙም ለሕዝብ እና ለሀገር ነው። የቀደመውን ታሪክ እና ታላቅነት ለመመለስ በአንድነት እና በፍቅር ሰላማዊ በኾነ መንገድ መሥራት የዚህ ዘመን ትውልድ አደራ ነው።
በታርቆ ክንዴ #amico

11 months ago