Logo
Tigu S Alemayew
ወንድሜ ሞተብኝ
የእናቴ ልጅ ገና በወጣትነቱ ሞተብኝ
ወንድሜ ብርሃንዬ ምንም ሳይሆን ማታ ላይ ፀሎት ወደሚያደርግበት ክፍል ለፀሎት ገብቶ በዛው ሞተብን 🥹💔
በልጅነቱ ከተወለደ ጀምሮ ለደብረሊባኖስ ገዳም ተሰቶ በዛው ተምሮ ተምሮ በዛው አድጎ በዛው ሞተብኝ
ያለፉት 9 ቀኖች ለቤተሰባችን በጣም ከባድ ሀዘን ነበር .. እንደአይን ብሌናችን የምንሳሳለት ወንድማችን , ለሰው እንኳን ወንድማችን ነው ብለን ለማውራት የምንፈራለት የምንሳሳለት ወንድማችን አጣነው....

የደብረሊባኖስ ገዳም እና የእኛ ቤተሰብ ታሪክ የሚጀምረው እንደዚህ ነው ... አያቴ እናቴን በወለደች በ 20 ቀኗ ባለቤቷ ድንገት ሲሞትባት እናቴ ሶስት ወር ሲሆናት ለአያቷ ሰታት እሷ በ 17 አመቷ ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም ሂዳ ምንና መንኩሳ ከ 60 አመት በላይ በቆብ ( በምንኩስና) ገዳሙን በፈታይነት እንዲሁም ሌሎች በገዳሙ ሴቶች ሊሰሩት የሚችሉትን እየሰራች እና ገዳሙን እያገለገለች ኑራ ነበር ... አባቴ ደሞ በደርግ ጊዜ በስራ ምክንያት የተለዩ ክፍለሀገራት ይሄድ ነበር እናቴንም ልጆቹንም ይዞ ነው ስሄድ እና እየሰራ ሲኖር የነበረው የኔ ታላላቆች የተለያየ ቦታ ነው የተወለዱት ይህ ወንድሜ በሰሜን ሸዋ ፍቼ ነው የተወለደው ከዛ በኃላ አባቴ ከልጆቹ አንድ ሰው ቤቤተክርስትያን እንዲያድግ ምኞቱ ስለነበረ ሁላችን ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም አያቴ ጋር እየሄድን እና እየተቀመጥን ፊደል ቆጥረናል እኔም በዜማ መምህር በነበሩት በየንታ መርአዊ ወንበር ስር ተቀምጬ እስከ መዝሙረ ዳዊት ድረስ በግዕዝ ተምሬጨርሼ ነው ከዛ ወደዘመናዊ ትምህርት የገባሁት ...ወንድሜ ብርሃኑ ግን ከ አራት አመቱ ጀምሮ በገዳም ሊማር እንድሄደ በዛው እየቀጠለ እየቀጠለ እድሜውን ሙሉ ተምሯል , ከዚህ በታች ያለውን ስርአተ ፍትሀቱ ላይ አባቶች ካነበቡለት ከመሰከሩለት ከህይወት ታሪኩ ላይ ነው የወሰድኩትኝ ...

እድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ወደዚህ ታላቁ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም መጥተው በመጀመሪያ ደረጃ የንባብ ትምህርታቸውን
ከመምህር አባ ኢያሱ አሰፋ ጉባኤ ቤት በመግባት በልዩ ኹኔታ መዝሙረ ዳዊቱን በቃል ጭምር አጠናቀው ተምረዋል፡፡
በመቀጠልም በዚሁ ገዳም ውስጥ ስመጥርና አንጋፋ ከኾኑት ከአለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ጉባኤ ቤት በመግባት ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምረው ጾመ ድጓ እና ድጓ አጠናቀው
በሚገባ ተምረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ከታላቁ ሊቅ የተክሌ አቋቋም መምህር ከኾኑት ከየኔታ በትረ ማርያም ገ/መድኅን የተክሌ አቋቋምን በመምህርነት ደረጃ በሚገባ አጠናቀው ተምረዋል፤ የቅኔ ሰዋስው ትምህርትንም ከመምህራን ቀጽለዋል፡፡

ክቡር አጋፋሪ ብርሃኑ እነዚህን ሁሉ ትምህርቶች ተምረው ለዚህ ሁሉ ሊቅነት ምሁርነትና ተጠያቂነት ያበቃቸው የእናታቸው የወይዘሮ ፍሬሕይወት ታፈሰ በጎ ምኞት ቅን አመለካከትና
የከፈሉት ታላቅ የእናት መሥዋዕትነት የአያታቸው የእማሆይ ብዙነሽ ታሃለው ጥብቅ ክትትል፣ ጥረትና ጸሎት ሲኾን ክቡር አጋፋሪ ብርሃኑ የዜማ ትምህርታቸውን ተምረው ገብተው
በልጅነት ጎናቸው አርፋለሁ ሲሉ አያታቸው እማሆይ ብዙነሽ የመጣኸው ለትምህርት እንጅ ለመኝታ መች መጣህ? እያሉ ከገድል ቤቱ በንባብ ከቅኔ ማሕሌቱ አገልግሎት እንዳይለዩ
አድርገው ተከታትለው ስላስተማሯቸው ነው፡፡
በዚህ መልኩ በመንፈሳዊ አገልግሎት በክርስትና ሕይወት አምረውና አሸብርቀው ከአደጉ በኋላ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች ላይ ተመድበው አገልግለዋል፡፡
ከሁለት ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በቅኔ ማሕሌቱ በኩል በአጋፋሪነት ማዕርግ ተመድበው የቦታውን ይትበሃል ከታላላቆች የቦታው ሊቃውንት ከአለቃ መርዓዊ
ሣህለ ሚካኤል እና ከየኔታ በትረ ማርያም ገ/መድኅን በማጥናት ብሎም በእጃቸው ጭምር በመጻፍ ለቦታው የይትበሃሉ ተጠያቂ የሥርዐተ ማሕሌቱ መሪ በመኾን
ሥርዐቱን በመጠበቅና በማስጠበቅ ከሊቃውንቱ ጋር በመከባበርና በመፈቃቀር ረጅሙን ዓመት በሚገባ
· አገልግለዋል፡፡

ክቡር አጋፋሪ ብርሃኑ ከዐሥር ዓመት የአጋፋሪነት ማዕርግ አገልግሎት በኋላ በሌሎች ልዩ ልዩ ሥራዎች ላይ እያገለገሉ በቅኔ ማሕሌቱ በኩልም የማሕሌቱ ኮከብ የሊቃውንቱ ጌጥ
የዝማሜው ውበት ነበሩ ከዚህ የተነሳ ሊቃውንቱም አጋፋሪ ይዝመመው አጋፋሪ ይወርበው፣አጋፋሪ ያንብበው ይሏቸዋል፣ እርሳቸውም ቢቃኙ፤ቢዘሙ፤ቢወርቡ ቢያነብቡ የማይሰለቹ
አንደበተ ርቱዕ አንደበተ ቀልጣፋ ድንቅ፣ ታላቅ፣ ሊቅና ምሁር ነበሩ፡፡
ከሁሉ የበለጠ ጸጋና ስጦታም አላቸው ለተራበ የሚያበሉ ለተጠማ የሚያጠጡ ለታረዘ የሚያለብሱ ካዘነው ጋር አዝነው የሚያረጋጉ ከተደሰተውም ጋር የሚደሰቱ ርኅሩኅ ታማኝ ሰው ወዳጅ ወንድም ነበሩ፡፡ " ....

ወንድሜ ገና ልጅ ነው እድሜው ከ 39 ወደአርባ እየሄደ ነበር ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ወቶ እዚህ አዲስ አበባ የተለያዩ አድባራት እንዲሁ በአሜሪካ ያሉ አድባራት ላይ እንዲያገለግል የተለያዩ እድሎች መተውለት ቢጠየቅም በተደጋጋሚ አልፈልግም ገዳሙን ትቼ አልወጣም በማለት ኑሯል እኛ ፕሮግራም እንኳን ኑሮን አዲስ አበባ ከመጣ አንድ ቀን ብቻ አድሮ ነው የሚሄደው ከገዳሙ መለየት በፍፁም አይፈልግም ነበር .. ወንድሜ በድንግልና የኖረ መናኝ ነበር በሚቀጥሉት አመታቶች ላይ መንኩሶ ዻዻስ የሚሆን እና እረጅም አመት ኑሮ እኛን እህት እና ወንድሞቹን ሁሉ ቀብራችንን አሳምሮ ከዛ በኃላ ይሞታል ብዬ የማስበው ወንድሜ ሰስቼው ለሰው የማላወራው ወንድሜ አንደተለመደው የቀን ውሎውን በሰላም ውሎ ሁሌ ከመተኛቱ በፊት እንደሚያደርገው ሊፀልይ ወደ ፀሎት ክፍሉ እንደገባ ሞተብኝ 💔 ሳላስታምመው ምንህን ነው ወንድሜ ሳልለው በቃ እንዲሁ ቀረብኝ 🥹💔
በጣም እረጅሙ ቆንጆው ባለግርማ ሞገሱ የእግዚአብሔር አገልጋይ የእግዚአብሔር ባሪያ .. ያ እኔ እንዲሆንልኝ እንዲሳካልኝ የሚፀልይልኝ ወንድሜን ጨክኜ ቀብርኩት

7 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.