Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በአዳማ ከተማ በሽርክና አብራት በምትሰራው ባልደረባዋ ላይ የአሲድ ውሀ የደፈችው ግለሰብ ተያዘች
 
በአዳማ ከተማ ደበላ ክፍለ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ በጋራ በመሆን ዳይመንድ የማሳጅ አገልግሎት አቋቁመው ሲሠሩ በቆዩ ሁለት ወጣቶች መካከል በተፈጠረ የገንዘብ አለመግባባት  ባለደረባዋ ላይ የአሲድ ውሀ የደፈችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና መምሪያ አስታውቋል።
 
መብራቴ ጅሬኛ እና ኬርያ እንድሪስ የተባሉ ሃያዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ወጣቶች ቀደም ሲል በነበራቸው የሥራ ልምድ ተነሳስተው በ2018 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ገንዘባቸውን በማዋጣት ሥራውን ጀምረው በሂደቱም ስኬታማ በመሆን ሌሎች ሁለት ሴት ሠራተኞችን ጭምር ቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል።
 
ይሁን እንጂ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ በገንዘብ ወጪ ዙሪያ አለመግባባት መፈጠሩን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና መምሪያ የኮሚኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታምራት ጌታሁን ለብስራት ሬድዮ ገልጸዋል።

ሁኔታው እየባሰ ሲሄድም መብራቴ መግባባት ካልቻልን ገንዘባችንን ተካፋለን በተናጠል እንሥራ የሚል ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን በኬርያ በኩል ግን ፈቃደኝነት ባለመኖሩ አለመግባባቱ እስከ ድብድብ ደርሶ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ አስማምቷቸው እንደነበር ተነግራል።
 
የሰፈነው ስምምነት ለቀናት እንኳን ሳይዘልቅ በነበረ የገንዘብ ጫና ውዝግብ ኬርያ ቀደም ሲል በያዘችው ቂም በስልክዋ ስትጫወት በነበረችው መብራቴ ላይ ከፍተኛ የአሲድ ውሀ በጭንቅላቷ ላይ ደፍታባታለች።
 
ጉዳቱን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ በሰጠው ፈጣን ትብብርና በፖሊስ ርብርብ ተጎጂዋ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተወስዳለች።ተጠርጣሪዋም በቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን ፖሊስ ጉዳዩን አጣርቶ ለፍትህ እንደሚያቀርብ ኮማንደር ታምራት ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

በትግስት ላቀው
#ዳጉ_ጆርናል Photo
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.