Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
በኢትዮጵያ የአፍና የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች እጥረት መኖሩ ተገለፀ

በአገሪቱ የአፍና የጥርስ ጤና ችግሮች በስፋት የሚታዩ ቢሆንም በዘርፋ የህክምና ባለሙያዎች እጥረት መኖሩን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ አስታውቋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ከሚስተዋሉ የጥርስ ጤና ችግሮች መካከል በዋናነት የህፃናትና የአዋቂዎች ጥርስ መበስበስ፣ የድድና የጥርስ አቃፊ አጥንት ሕመም፣ የጥርስ መርገፍ እንዲሁም የአፍና የከንፈር ካንሰር ይገኙበታል።

በሆስፒታሉ የጥርስና ማክሲሎፌሻል ትምህርት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የፊትና መንጋጋ ቀዶ ጥገና ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አዲስ ካሳሁን ከብስራት ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ጥርስን እስከ ማጣት ሊያደርስ የሚችለው የድድና የጥርስ አቃፊ አጥንት ህመም 18.7 በመቶ ስርጭት ሲኖረው የጥርስ መርገፍ ደግሞ 1.8 በመቶ ስርጭት እንዳለው  ተናግረዋል።

የሕክምና ኮሌጁም ከመደበኛው የጥርስ ህክምና በተጨማሪ የአፍ፣ የመንጋጋና የፊት ቀዶ ጥገና ሕክምናን እንደሚሰጥ ገልጿል።ተቋሙም በየቀኑ ከ90 እስከ 140 የሚደርሱ ታካሚዎችን በማስተናገድ ሕክምናን እየሰጠ መሆኑን ዶክተር አዲስ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በፈረንጆቹ 2022 የታተመውና በ2018 አ/ም የተሰበሰበው መረጃን ያካተተው የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በኢትዮጵያ የሚገኙት 1 ሺህ 745 የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ብቻ ናቸው።በዘርፋ የተሰማሩ የባለሙያዎችን ቁጥር አስመልክቶ ወቅታዊና የተጠናቀረ መረጃ ባለመኖሩ በአሁኑ ወቅት ያለው ቁጥር ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችልም ዶክተር አዲስ ገልጸዋል።

በሰብል አበበ
#ዳጉ_ጆርናል
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.