Logo
AHADU RADIO FM 94.3
ዘምዘም ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ 22 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ

👉 ባንኩ "ዘምዘም ሪሚት" የተሰኘ ዲጂታል የሐዋላ አፕሊኬሽን ይፋ አድርጓል

ዘመዘም ባንክ በአምስት ዓመት የስራ ጉዞ ውስጥ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ 22 ቢሊዮን ብር መድረሱን እና 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ደንበኞችን ማፍራቱን አስታውቋል ።

ባንኩ ይህንን ያስታወቀው መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም "በማይነጥፍ ጽናት ወደ ላቀ ምዕራፍ " በሚል መሪ ቃል አምስተኛ የስራ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ነው ።

ባንኩ በአምስት ዓመት የስራ ጉዞ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አማራጮችን በማስፍት ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን በማሳደግ እና የሸሪዓ መርሆችን በመከተል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ ተጨባጭ ዕድገት ማስመዝገቡን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መሊካ በድሩ ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 31 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን የባንኩ የቅርንጫፍ ቁጥር 141 መድረሱን አክለው ገልፀዋል ።

ከዚህ በተጨማሪም የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 5.6 ቢሊዮን ብር እንደደረሰና የፋይናንስ አቅሙን እንዲሁም የዕድገት መሰረቱን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደቻለ ተገልጿል ።

ባንኩ በቀጣዮቹ ዓመታት የዲጂታል ለውጡን በማፍጠን እና የደንበኞችን ችግር የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሻሻል እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብሩን በማጠናከር በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በወለድ ነፃ ባንክ ለማሳደግ እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አብራርተዋል ።

የአምስተኛ ዓመት አከባበሩን አስመልክቶ "ዘምዘም ሪሚት" የተሰኘ ዲጂታል የሐዋላ አፕሊኬሽን ይፋ አድርጓል።

በተመስገን ተጋፋው

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.