Logo
FastMereja
የኢትዮጵያ የፈጠራ ባለሙያዎችን ለዓለም አቀፍ መድረክ የሚያበቃው «አደይ አዋርድ»ሊካሄድ ነዉ!
#fastmereja :-በኢትዮጵያ በዘመናዊ፣ ኮንቴምፖራሪ እና ተሞክራዊ (experimental) ክንውን ጥበባት ዘርፍ የተሰማሩ የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታትና ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀው «አደይ ኮንቴምፖራሪ አርት አዋርድ» (Adey Contemporary Art Award) ጥቅምት 07 ቀን በአድዋ ድል ሙዚየም በደመቀ ሁኔታ እንደሚካሄድ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

«የኢትዮጵያ የፈጠራ ጥበባት አዲስ ገፅታ» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፤ በአካላዊ ቲያትር አዘጋጅና ጸሐፊ አርቲስት ተክሉ አሻግር (ሔኖክ) ሀሳብ ጠንሳሽነት፣ በጂ ኤይት ኢንተርቴይመንትና ፕሮሞሽን እና በኢተርናል ሚዲያ ኮሙኒኬሽን እንዲሁም በአዲስ ሚዲያና ኔትወርክ አጋርነት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ መርሃ-ግብር በሀገራችን በበቂ ሁኔታ ትኩረት ያላገኙ አዳዲስ የፈጠራ ዘርፎችን ወደ ፊት ለማውጣትና ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን፤ በስድስት ዋና ዋና የኪነ-ጥበባት ትዕይንታዊ ክንውን ዘርፎች በስሩ ባቀፋቸው 19 የተለያዩ የጥበብ መስኮች ለተሰማሩ ባለሙያዎች ዕውቅና ይሰጣል።

ከነዚህም መካከል ዘመናዊ ሰርከስ፣ ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ ዘመናዊና ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ (ዲጄዎችን ጨምሮ)፣ ፋሽንና ሞዴሊንግ፣ ስዕልና ቅርጽ፣ አጭር ፊልም እንዲሁም ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አንጋፋ ባለሙያዎች የሚሰጥ የህይወት ዘመን ሽልማት (Lifetime Award) ይገኙበታል።

የእጩ ጥቆማ ሂደቱ መጠናቀቁን ያረጋገጡት አዘጋጆቹ፤ አሸናፊዎችን ለመለየት የሚያስችለው ይፋዊ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአዋርዱ ድረ-ገጽ ላይ መጀመሩን ተገልፆ በዚህም መሠረት አሸናፊዎች 60 በመቶ በህዝብ ድምፅ እና 40 በመቶ በባለሙያ ዳኞች በሚሰጥ ነጥብ እንደሚለዩም በመግለጫዉ ተገልጿል።

በአድዋ ድል ሙዚየም በደመቀ ሁኔታ በሚከናወነው በዚህ ፕሮግራም ላይ የአደይ አበባ ምንጣፍ ሥነ-ሥርዓት፣ የስዕልና ቅርፃ ቅርፅ ኤግዚቢሽን፣ የሰርከስና የዳንስ ቅንብርትርኢቶች፣ በአዱኛ ዳንስ ግሩፕ የሚቀርብ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመድረክ ሥራ፣ የፋሽን ሾው፣ የዘመናዊ ሙዚቃ ዝግጅቶች እንዲሁም የኔትወርኪንግና የዲጄ ምሽት እንደሚኖር ተመልክቷል።

ዝግጅቱን ከዘንድሮው የመክፈቻ ፕሮግራም በኋላ በየዓመቱ መስከረም 30 ቀን በቋሚነት ለማካሄድ የታቀደ ሲሆን፤ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ደግሞ ለአሸናፊዎች ለቀጣይ ስራዎቻቸው የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ (Grant) ለማመቻቸት ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ንግግር እየተደረገ እንደሚገኝም ነዉ የተገለፀዉ።

9 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.