Logo
YenetaTube
በሰሜን ሸዋ ከ25 ሚሊዮን በላይ የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ስጋት ደቀነ፤ በኬሚካል እና በባህላዊ መንገድ የመከላከል ዘመቻ ተጀመረ

በሰሜን ሸዋ ዞን በርካታ ወረዳዎች ውስጥ ግምቱ ከ25.9 ሚሊዮን በላይ የሆነ አደገኛ የግሪሳ ወፍ መንጋ መከሰቱ ተገለጸ።

አደጋውን ለመቀነስና በሰብል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመታደግ ሰፊ የመከላከል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል።

እንደ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ መረጃ፤ መንጋው በተለይም በኤፍራታ፣ አንፆኪያ፣ ሸዋሮቢት፣ ቀወት፣ ምንጃር እና በረኸት ወረዳዎች በስፋት ታይቷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ታደሰ ማሙሻ እንደገለጹት፣ አደጋውን ለመቆጣጠር የዞኑ ባለሙያዎች ከክልል እና ከፌደራል የግብርና አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ስፍራው ተሰማርተዋል።

ወፉ ድንበር ተሻጋሪና መንጋውም እጅግ ዘርፈ-ብዙ በመሆኑ፣ አደጋውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመግታት በብቸኝነት የአየር ላይ ኬሚካል ረጨታ ስራ ተጀምሯል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት በአንፆኪያ፣ ኤፍራታ እና ምንጃር ወረዳዎች የተካሄደው ረጨታ ስኬታማ ውጤት ያመጣ ሲሆን፤ በሸዋሮቢት እና ቀወት አካባቢዎች ደግሞ ረጨታውን የሚያፋጥን የአውሮፕላን ማረፊያ (Air Strip) የማዘጋጀት ስራ በመጠናቀቅ ላይ ነው።

ከአየር ላይ የመከላከል ስራው አርሶ አደሩ ሰብሉን ለመጠበቅ ባህላዊ ዘዴዎችን እንዲጠቀም ጥሪ ቀርቧል።

አርሶ አደሮች በህብረት በመሆን በጩኸት፣ በቆርቆሮ ድምፅ እና በተለያዩ ባህላዊ ስልቶች ወፉ በሰብል ላይ እንዳያርፍና ውድመት እንዳያደርስ እንቅስቅሴ እንዲያደርጉ ተመልክቷል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ እንደጠቆመው፣ የመንጋው የመስፋፋት አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ከፌደራል ተቋማት ጋር የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

13 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.