Logo
TIKVAH-MAGAZINE
አሜሪካ ለሶማሊያ ሰላም አስከባሪዎች የሚደረገው የሎጅስቲክስ ድጋፍ የሚቆምበትን ጊዜ አራዘመች

አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያ ድጋፍ ቢሮ (UNSOS) በኩል ለአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (AUSSOM) የሚደረገውን የሎጅስቲክስ ድጋፍ ለማቋረጥ የያዘችውን የጊዜ ገደብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለማራዘም ተስማምታለች።

አሜሪካ ለዲፕሎማቶች ባሰራጨችው ረቂቅ ሰነድ መሠረት፣ በሶማሊያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድጋፍ ቢሮ ለአንድ ዓመት በሚቆይ የደረጃ በደረጃ ቅነሳ ሂደት አልፎ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ተስማምታለች።

ይህ ውሳኔ ድጋፉ እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2026 ማብቂያ ላይ በድንገት ይቋረጣል ተብሎ የተደቀነውን ስጋት ያስቀረ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋሺንግተን ወደፊት ቢሮውን ሥራ በገንዘብ እንደማትደግፍ ገልጸው፣ የቅነሳው ዝርዝር ሂደት በታህሳስ ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንደሚወሰን አስረድተዋል።

ቢሮው በየዓመቱ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ በጀት ያለው ሲሆን፣ ለአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች የምግብ፣ የውሃ፣ የነዳጅ፣ የሕክምና እና የትራንስፖርት አቅርቦቶችን ያመቻቻል።

የደህንነት ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የሎጅስቲክስ ድጋፉ መቋረጥ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይልን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልና አል-ሸባብን በመታገል ላይ የሚገኘውን የሞቃዲሾ መንግሥት ሊያዳክም ይችላል የሚል ስጋት አስቀምጠዋል።

አሜሪካ ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች 75 በመቶ በጀት እንዲሸፍን የቀረበውን የፋይናንስ መዋቅር ዕቅድ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

ዘገባው የሮይተርስ ነው።

@TikvahethMagazine
24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.