በፈርዖኖቹ ሚዛን፤ ኢትዮጵያ አትመዘንም!
የካይሮ ፖለቲከኞች የለመዱትን የዛቻ እና የለቅሶ ዜማ መልሰው ሲያዜሙት መስማት አዲስ ነገር መሆኑ ቀርቷል።
ሰሞኑን የግብፅ መስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስትር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን “ሕገ-ወጥ” ሲሉ ፈርጀው፣ “ብሔራዊ የውሃ ደህንነታችንን ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብታችን የተጠበቀ ነው” ሲሉ በቁጭትና በትዕቢት መካከል የተሰነቀረ መግለጫ ሰጥተዋል።
ይህ አባባል ግን በበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ሚዛን ሲመዘን፣ ሌሊት አልፎ ቀን በፈነጠቀበት ዘመን የሚቃዥ የትላንት ሕልመኛ ሰንካላ ምክንያት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።
የፈርዖኖች ምድር ፖለቲከኞች አሁንም ድረስ ዓለም የተቀየረች አይመስላቸውም። በቅኝ ግዛት ዘመን የተጻፉና ኢትዮጵያ ያልፈረመችባቸውን ያረጁ የውሃ ክፍፍል ስምምነቶች እንደ ሕግ እየቆጠሩ፣ “ታሪካዊ መብታችን አልተከበረም” ብሎ መጮህ ራስን ማታለል ነው።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በአካል ተጠናቅቆ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በጀመረበትና የካይሮን የዛቻ ‘ማዕበል’ በዲፕሎማሲያዊ እና በሳይንሳዊ እውነታዎች ባፈረሰበት በዚህ ወቅት፣ ግድቡን “ሕገ-ወጥ” ብሎ መጥራት የተጨባጩን ዓለም እውነታ ከመካድ የሚመጣ የፖለቲካ ቅዥት ነው።
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለው በካይሮ ፈቃድ ወይም በፓሪስና ለንደን የቅኝ ግዛት ውሎች አይደለም። ግድቡ በኢትዮጵያውያን የደም፣ የላብ እና የእንባ ጠብታ የተገነባ የሉዓላዊነት ሐውልት ነው።
እያንዳንዱ የኮንክሪት ክምችት፣ እያንዳንዱ የስባሪ ሳንቲም መዋጮ እና የሕዝባችን ቁርጠኝነት ያቆመው እውነት እንጂ በካይሮ ጠረጴዛ ላይ በሚፈረም የይሁንታ ወረቀት የሚጸድቅ የልመና ፕሮጀክት አይደለም።
ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጨለማ ለማውጣት የምታደርገው ጥረት በማንም ሀገር ፈቃደኝነት ላይ አይንጠለጠልም።
ግብፅ ለዓመታት በዓባይ ውሃ ላይ ብቻዋን ስትደሰትና ስታባክን፣ ኢትዮጵያ ግን 85 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ምንጭ እያመነጨች በጨለማ ስትማቅቅ መኖሯ የታሪክ መዛባት ነበረ። ዛሬ ያ የታሪክ መዛባት በኢትዮጵያውያን ክንድ ታርሟል። ካይሮ ይህንን እውነት “የተጠናቀቀ እውነታ” ብላ ለመቀበል መቸገሯ የራሷ የፖለቲካ ሥነ-ልቦና ቀውስ እንጂ የኢትዮጵያ የቤት ሥራ ሊሆን አይችልም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና ሕልውና በአንድ ወንዝ ፍሰት ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ዛሬ የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ቁመና በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር በሁለቱ ወሳኝ ውሃዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
ዓባይ የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ትንሳኤ፣ የኢንዱስትሪ ልማት እና የብርሃን ምንጭ ሲሆን፤ ቀይ ባሕር ደግሞ የውጭ ንግድ፣ የቀጣናው ስትራቴጂካዊ ተጽዕኖ እና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ማማ ነው። እነዚህ ሁለት ውሃዎች የኢትዮጵያ የሕልውና ሁለት ገፆች በመሆናቸው አንዱ ለአንደኛው ዋስትና ነው።
ግብፅ በዓባይ ላይ የምታሳየው እምቢተኝነት እና የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና የማመስ ፍላጎት፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ስትራቴጂካዊ የባሕር በር ይዞታ ይበልጥ እንድታጠናክር የሚያስገድዳት እንጂ ወደኋላ የሚያስፈገፍጋት አይደለም።
ካይሮ ፈረሶቿን ጋልባ በኢትዮጵያ ጓሮ ለመቅበዝበዝ የምታደርገው ሙከራ፣ የዚሁ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ውሃዎች መካከል የተዘረጋውን የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ የበላይነት ለመቀነስ የሚደረግ አቅመ-ቢስ መወራጨት ነው።
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ ያቀረቧቸው ቁጥሮች የራሳቸውን ስግብግብነት የሚያጋልጡ እንጂ ለኢትዮጵያ ወቀሳ ሊሆኑ አይችሉም። እርሳቸው እንዳሉት የግብፅ ዓመታዊ የውሃ ኮታ 55.5 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን በየዓመቱ በቢሊየኖች የሚቆጠር የዝናብ ውሃ ታገኛለች ይላሉ። ይህ ትልቅ የፖለቲካ ስላቅ ነው!
ተፈጥሮ የሰጠንን የዝናብ ውሃ እየቆጠሩ፣ እኛ ግን ከምንጩ የሚመነጨውን ወንዝ እንዳንነካ መከልከል ምን ይባላል?
ዝናብ ስለዘነበ ብቻ አንድ ሀገር የተፈጥሮ ወንዟን የመጠቀም መብቷ ይገፈፋልን? ግብፅ በረሃ ላይ ተቀምጣ፣ የዓባይን ውሃ ብቻ ሳይሆን በከርሰ-ምድር ውስጥ ያለውን ግዙፍ የውሃ ክምችት እና የባሕር ውሃ ማጣሪያን መጠቀም እየቻለች፣ የኢትዮጵያን የልማት ሕልም በውሃ ጥማት ሰበብ ለማገት መሞከሯ ፍጹም ስግብግብነት ነው።
ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ ግልጽ ነው፦ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም። የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ፣ የራሷን ሕዝብ ከድህነት የመታደግ መብቷን ትጠቀማለች። ካይሮ ግን “የእኔ ብቻ ካልሆነ” በሚል የድሮው የባለቤትነት መንፈስ “ሕጋዊ ስምምነት” እያለች የምታቀርበው ሰነድ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠፍነግ የሚደረግ ሴራ ስለሆነ ፍጹም ተቀባይነት የለውም።
የካይሮ ፖለቲከኞች የዛቻ መግለጫዎችን ማውጣት እና ግድቡን “ሕገ-ወጥ” ማለታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ለውስጥ ፖለቲካቸው ፍጆታና ለሕዝባቸው ማስተገሻ ፕሮፓጋንዳ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን በምድር ላይ ያለው እውነታ አይቀየርም።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ የቁርጠኝነት ሐውልት ሆኖ ዓባይን እየገደበ፣ ብርሃን እየፈነጠቀ ይኖራል። ኢትዮጵያ በዓባይ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላት ብሔራዊ ጥቅም በማንም ዛቻ አይገታም። የካይሮ ስጋት የሚቀረፈው ወደ እውነት በመመለስ እና ከኢትዮጵያ ጋር በእኩልነት መርህ ላይ በመነጋገር እንጂ፣ ያረጀ የቅኝ ግዛት ሕልምን እያዩ “እርምጃ እወስዳለሁ” በሚል የድሮ ፉከራ አይደለም።
የዓባይ ውሃ በካይሮ ፈቃድ አይፈስም፤ የኢትዮጵያ ልማትም በፈርዖኖች ሚዛን አይመዘንም።
በኃይለኢየሱስ መኮንን

16 days ago