Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የጉግል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሞዴል የሆነው ጀሚናይ፣ የሳይበር ደህንነት አቅሙ እየተፈተነ ባለበት ወቅት፣ ያለ ማንም ሰው ትዕዛዝ ራሱን ችሎ ሦስት ኩባንያዎችን ጠልፎ (Hack አድርጎ) መግባቱን ኩባንያው በይፋ አረጋገጠ። ቢቢሲ ከጉግል ኃላፊዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፣ ጀሚናይ በበይነ-መረብ ላይ የሚገኙ ክፍት መረጃዎችን በማሰባሰብ እና የይለፍ ቃላትን በራሱ በማሰላሰል እና በመገመት ነው የኩባንያዎቹን ድረ-ገጾች ሰብሮ የገባው። ምንም እንኳን ሞዴሉ የኩባንያዎቹን መረጃ ካገኘ በኋላ ጥቃቱን ራሱ ቢያቆምም፣ ድርጊቱ ግን በቴክኖሎጂው ዓለም ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል። የጉግል የደህንነት ምሕንድስና ምክትል ፕሬዝዳንት ሄዘር አድኪንስ፣ ኩባንያዎቹ ስለደረሰባቸው የሳይበር ጥቃት እንዲያውቁ መደረጉን ጠቅሰው፣ ይህ ክስተት ኃያል የሆኑ የኤአይ (AI) ሥርዓቶችን በኃላፊነት ማሰልጠን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦፕን ኤአይ እና የአንትሮፒክ የክሎድ የኤአይ ሞዴሎችም በተመሳሳይ ራሳቸውን ችለው የሳይበር ጥቃቶችን ፈጽመው እንደነበር መገለጹ የሥጋቱን መጠን አባብሶታል። የቴክኖሎጂው አደጋ እያየለ በመምጣቱ፣ የኦፕን ኤአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳም አልትማን ጉዳዩን አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማብራሪያ ሊሰጡ ቀጠሮ ይዘዋል።

እዚህ ጋ ቆም ብለን የነገዋን ዓለም አቅጣጫ እናስብ! አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አሁን ላይ "ረዳት" ከመሆን አልፎ "አስፈጻሚ" ወደሚሆንበት የከፍታ እና የአደጋ ጠርዝ ላይ ደርሷል። ጀሚናይ ራሱን ችሎ የይለፍ ቃል ገምቶ ኩባንያዎችን ሲጠልፍ፣ የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች እንኳ አስቀድመው ያልጠበቁት እና ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ያልቻሉት አቅም መፈጠሩን ያሳያል። የኤንቪዲያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄንሰን ሁዋንግ "በቴክኖሎጂው ልማት በተቻለን ፍጥነት መገስገስ አለብን" ቢሉም፣ ይህ ያለ በቂ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የደህንነት ቁጥጥር የሚደረግ የትርፍ እሽቅድምድም፣ የሰው ልጅን መጻኢ ዕድል ለማይታወቅ አደጋ አሳልፎ የሚሰጥ የዕውር ድንብር ጉዞ ነው።

ቴክኖሎጂ ሥነ-ምግባር እና ጠንካራ የቁጥጥር ልጓም ከሌለው፣ ከበረከትነቱ ይልቅ እርግማኑ ያመዝናል! የኤአይ ፈጣሪዎች የገንዘብ እና የገበያ ፉክክራቸውን ትተው፣ እነዚህ ኃያል ማሽኖች ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ ወጥተው ዓለምን ወደ ቴክኖሎጂያዊ ትርምስ ከመክተታቸው በፊት ጠንካራ ዓለም አቀፍ የደህንነት ሕግ ሊያበጁላቸው ግድ ይላል!

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ከቁጥጥር ውጭ መውጣት የሰው ልጅ የመጨረሻው አደጋ ይሆናል ብላችሁ ትሰጋላችሁ ወይስ የተለመደ የቴክኖሎጂ እድገት ሂደት ነው? ኮመንት ላይ እንወያይበት።

19 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.