Logo
YenetaTube
አበሽጌ ወረዳን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማጠቃለል የታሰበ ሴራ መኖሩን አብን አስታወቀ

በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ማፈናቀልና ንብረታቸውን ለአመራሮች የመከፋፈል አደገኛ ሁኔታ በማስመልከት ከአብን የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን መዋቅራዊ የዘር ማፅዳት የሕዝብ ቁጥር ስብጥር የመቀየር የጅምላ አፈና እና የህልውና ስጋት ላይ የመጣል የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማስመልከት ከባድ የአቋም መግለጫ አውጥቷል ንቅናቄው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳና ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም በአዋሳኝ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ጅማ ዞኖች በታጠቁ ኃይሎችና በአካባቢው የአስተዳደር መዋቅር ጭምር በቅንጅት ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ገልጿል

ይህ ጥቃት ተራ የፀጥታ መደፍረስ ሳይሆን በአካባቢው ለዘመናት የሚኖረውን የአማራ ማህበረሰብ ከቀዬው በማፈናቀል መሬትና ንብረቱን በመንጠቅ የአበሽጌ ወረዳ አስተዳደራዊ ወሰኖችን በኃይል የመለወጥ አደገኛ ስትራቴጂ አካል ነው ብሏል በምዕራብ ሸዋና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የአማራ ተወላጆች ከተፈናቀሉ በኋላ የመሬት ይዞታቸው ለየደረጃው አመራሮችና አጋር ባለሀብቶች እየተከፋፈለ እንደሚገኝና ዋና አላማውም አበሽጌ ወረዳን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማጠቃለል መሆኑን አብን አስታውቋል

በ2016 ዓ ም የካቲት ወር ማህበረሰቡ ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በመተባበር ቀጠናውን ከኦነግ ሸኔ ጥቃት ለመከላከል ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ከሽብር ቡድኑ ጋር ትስስር ያላቸው የፀጥታ አመራሮች የታጠቀውን መሳሪያ በመግፈፍ ህዝቡን ለጭፍጨፋ አጋልጠው ሰጥተዋል ብሏል በመቀጠልም በአመያ ወረዳ ቆታ እና በዳርጌ አካባቢዎች በኦሮሚያ አድማ ብተና እና በሸኔ ታጣቂዎች የተቀናጀ ጥቃት ከ54 በላይ ሕፃናት ነፍሰጡር እናቶች አርሶ አደሮች እንዲሁም በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ 6 መነኮሳትና 3 አገልጋዮች መጨፍጨፋቸውን መግለጫው ያረጋገጣል

ከሐምሌ 2016 ዓ ም ጀምሮ በወልቂጤ ከተማ እና በአበሽጌ ወረዳ የታፈሱ ከ1,000 በላይ ሰላማዊ የአማራ ተወላጆች ያለ ምንም ፍርድቤት ትዕዛዝ ታፍነው በወልቂጤ እና በዋልጋ ማሰቃያዎች ታስረው ኢሰብአዊ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ስቃይ ሲደርስባቸው መቆየቱ ተገልጿል ይህ አፈና ሆን ተብሎ በዋናው የእርሻና የክረምት ወቅት በመከናወኑ የተዘራው አዝመራ በየሜዳው እንዲበላሽ መደረጉንና በትራንስፖርት እገዳ ምክንያት አርሶ አደሩ ለተደራጀ የኢኮኖሚ ውድቀት መዳረጉን አብን አመልክቷል

በመንግሥት ጥሪ መሠረት ሰላምና ልማትን ሲያስከብሩ የነበሩ አርሶ አደሮችን ባለሀብቶችን እና ወጣቶችን ፋኖ ናችሁ በሚል የሐሰት ስም በመፈረጅ በሰላማዊው የአማራ ማህበረሰብ ላይ ሰፊና የተቀናጀ ማዋከብና የማጥቃት ዘመቻ መከፈቱን ንቅናቄው ኮንኗል በዚህ የጥቃት ሂደት ውስጥ ከአማራ ሕዝብ ባሻገር የጉራጌና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ በርካታ ንጹኃን ዜጎች የሁከትና የፖለቲካ ሴራ ሰለባ መሆናቸውን የገለጸው አብን ድርጊቱን በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል

ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት መዋቅር ራሱ የዜጎችን ሕጋዊ መሣሪያ በመገፈፍ ለታጣቂዎች ጥቃት ማጋለጡ ጥቃቱ የፖለቲካ ሥርዓቱ አካል መሆኑን እንደሚያሳይና የፌደራል መንግሥቱ ዝምታ ለድርጊቱ ይሁንታ መስጠት እንደሆነ ጠቅሷል

አብን በመግለጫው የፌደራል መንግሥት እና የደኅንነት መዋቅሮች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚያካሂዱትን መዋቅራዊ እስራት እና የእንቅስቃሴ ገደብ በአስቸቋይ እንዲያቆሙና በወልቂጤ እና በወልጋ ታስረው የሚገኙ ንጹሃን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል

በተጨማሪም የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የተወሰዱ የሕዝብ መከላከል መሣሪያዎች እና የተዘረፉ ንብረቶች በአስቸቋይ ለባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ አብን በጥብቅ ጠይቋል

በጅምላ ጭፍጨፋዎች እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ እጃቸው ያለበት የመንግሥት አመራሮች የፀጥታ አካላትና ታጣቂዎች ለፍትሕ እንዲቀርቡና የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ ገለልተኛ ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል

የአማራ ሕዝብ ከአካባቢው እህትና ወንድም የጉራጌና የኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለዘመናት የገነባውን ወንድማማችነት አጠናክሮ እንዲቀጥልና የጥቂት አክራሪ ፖለቲከኞችን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ በንቃት እንዲመክት አብን ጥሪ አስተላልፏል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የነጻ መርማሪዎች አጣሪ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የሚፈጸመውን የዘር ማፅዳት እንዲያጣራ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና እንዲያደርግ አብን ጠይቋል

በመጨረሻም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ለተበደሉና በሕገ-ወጥ መንገድ ለታሰሩ ወገኖች ፍትሕ እስኪረጋገጥ ድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በህዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙ አካላት በፍትህ አደባባይ መቆማቸው እንደማይቀር አስታውቋል

19 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.