Logo
EBC
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የተነጠቅነውን በዲፕሎማሲ የማስመለስ ጉዞ
********************
(የዕለቱ መልዕክት)

የባህር በር ጥያቄ ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከሃይማኖት፣ ከብሔር ወይም ከቡድን ፍላጎት በላይ የሆነ፤ ፍጹም ሀገራዊ እና የህልውና ጉዳይ ነው። ህልውና ሲባል እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል፤ የመኖርና ያለመኖር ወሳኝ ምዕራፍ ማለት ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ታሪካዊ ባላንጣዎች ሆን ብለው የፈጠሩት ጫና ውጤት መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም በከተማ ልማት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም ዘርፎች ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ይህ ዕድገት የባህር በር ቢታከልበት ኖሮ ከዚህ እጥፍ ማደግ ይቻል ነበር።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የባህር በር አልባ ሀገር ሳትሆን፤ ከውቅያኖስ ጋር የተቆራኘች ሀገር ነች። የኢትዮጵያን ጉዳይ ልዩ የሚያደርገው ታሪካዊ የባህር በር ባለቤት የነበረች ቢሆንም ከህዝቧ እውቅና እና ከዓለም አቀፍ ህግ ማዕቀፍ ውጪ በሴራ በሯ የተዘጋባት መሆኑ ነው።

ዛሬ ላይ እየተጠየቀ ያለው አዲስ በር እንዲከፈት ሳይሆን የተዘጋውን ታሪካዊ በር በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ ነው። ይህን ልዩ ታሪካዊ እውነታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተረዳው ሲሆን ከተወሰኑ ታሪካዊ ባላንጣዎች በስተቀር የኢትዮጵያን የባህር በር ባለመብትነትን የሚቃወም የለም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህር በርን በንግድ አግባብ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ጥያቄ ግን ከዚህ የዘለለ ታሪካዊና ሉዓላዊ መብትን መሰረት ያደረገ ነው።

ሞሮኮ ለጎረቤቶቿ በነጻ የባህር በር እንደሰጠችው ሁሉ አፍሪካ ውስጥ እንዲህ አይነት የትብብር አሰራሮች አሉ። ኢትዮጵያ የባህር በር እንድትጠቀምበት ቢፈቀድ ከኢትዮጵያ እኩል አልፎ ተርፎም የበለጡ ተጠቃሚ የሚሆኑት ራሳቸው የጎረቤት ሀገራት ናቸው።

ይህን እውነት በሚገባ የተገነዘቡ አካላት፣ ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል የረጅም ጊዜ ሴራ ሸርበዋል። ዛሬ በሀገር ውስጥ በየብሔሩ፣ በየጎሳው እና በየፖለቲካው የሚነሱ ግጭቶች እና መከፋፈሎች የዚሁ ሴራ አካል ናቸው።

የእነዚህ ኃይሎች ፍላጎት የተበታተነች፣ በርስበርስ ግጭት የምትታመስ እና ደካማ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድ ማየት ነው።

ስለዚህ ከጠባብ የብሔር እና የቡድን ጨዋታዎች በመውጣት ለሀገራዊ አንድነት እና ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። ሰላም የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ የዜጎች ሁሉ የጋራ ኃላፊነት ነው።

የባህር በር ጥያቄው ከምንጊዜውም በላይ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በጠረንጴዛ ዙሪያ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ዜጎችም የመከፋፈል አጀንዳን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ሊቆሙ ይገባል። የባህር በር የሀገር ህልውና ነው፤ ለሀገር ህልውና ደግሞ ሁሉም በአንድ ቋንቋ ሊነጋገር ይገባል፡፡

ኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

21 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.