Logo
YenetaTube
ቅዱስ ራጉኤል የልባችሁን መልካም መሻት ይሙላላችሁ🙏

የኪሩቤል አለቃቸው የጌትነቱ ዙፋን ጠባቂ🙏

የስሙ ትርጓሜ የኃያላን ኃያል እግዚአብሔር ማለት ነው። ከኃያላን ሁሉ በላይ ኃያል የሆነው እግዚአብሔር ኃያልነቱ ከ - እስከ የሌለው መሆኑን ለመግለጽ የተቀመጠ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ኃያል የኃያላን ኃያል መሆኑን የሚገልጽ ትርጉም አለው። ይህ ኃያል መልአክ ቅዱስ ራጉኤል ነው፡፡ አንድም ራጉኤል ማለት የብርሃናት አለቃ ማለት ነው። የብርሃናት አለቃ ሲባል ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን በማመላለስ ለሰው ልጆች፣ ለአዝርዕት፣ ለእንስሳት፣ ለአራዊት ሁሉ ብርሃንን የሚመግብ ነው ማለት ነው። አንድም ራጉኤል ማለት የሚበቀል ማለት ነው። በቀል የሚገባው ለጠላት ነው የሰው ልጅ ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፡፡ አንድም ራጉኤል ማለት ጽኑ እግዚአብሔር ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ጽኑነት ለማጉላት ሲል ጽኑ አለው። እግዚአብሔር የማይወላውል የማይዋዥቅ የማይከዳ ጽኑ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ ትርጉም ያለው ስያሜ ነው።

በብርሃናት ሁሉ ላይ የሰለጠነ መልአክም ነው። ከአዳም ሰባተኛ ትውልድ የሆነ በእግዚአብሔር ፊት ያማረ ሥራው የሰመረ እስከዛሬ የሞት ወጥመድ ያልያዘው ነብዩ ሔኖክ "ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነ ጠላት ዲያብሎስን የሚበቀለው ቅዱስ ራጉኤል በብርሃናት ላይ የሰለጠነ ነው" ይለናል፡፡ በመጽሐፈ ሔኖክ 6÷4 እንደተጻፈው ቅዱስ ራጉኤል እግዚአብሔርን አምነው ሕጉን ጠብቀው በፍርሐት አምልኮቱን ለሚፈጽሙ ሁሉ ጠላት ዲያብሎስን ያርቅላቸዋል ፈጥኖ በመድረስም ይታደጋቸዋል። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ64 ዓመቷ ካረፈች በኋላ ሥጋዋ ተነጥቆ በዕፀ ሕይወት ሥር ሲያርፍ አብሮ ለሔደውና ስጋዋን ሲያጥን ለነበረው ለፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ኅብስትን የመገበ መልአክ ነው።

ሎጥን፣ ሚስቱንና ልጆቹን ከእሳተ ገሞራ ያዳነ፣ የበለአምን እርግማን ወደ በረከት የለወጠ እርሱ ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ይቆጣጠር ዘንድ የሾመው ታላቅና ቅዱስ መልአክ ነው። አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለመተካት ዓለምን የመለወጥ ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ መልአክ ነው። ከእግዚአብሔር የጌትነት አዳራሽ ይገባና ይወጣ ዘንድ ስልጣን ያለው ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር በፈጣሪ የጌትነት ዙፋን ፊት የሚቆም ነው። በቅዱስ ራጉኤል ሥዕል ላይ የምናየው ይህ ባለ አራት ራስ ንስር ከአርባእቱ ኪሩቤል አንዱ ገጸ ንስር ነው። የሥላሴን የጌትነት ዙፋን የሚሸከሙ አርባዕቱ እንስሳት ናቸው። የሚሸከሙት ሲባል ጫማ የሰውን ልጅ እንደሚሸከመው እንጂ ችለውትስ አይደለም። እነርሱም የሰው፣ የእንስሳ፣ የንስርና የአንበሳ ገጽ ያላቸው ናቸው።

ቅዱስ ያሬድም በድጓው "አርባእቱ እንስሳ አልቄንጥሩ እንደሚባለው ንስር ፊት ለፊት አይታዩም አንዱም በመራቸው ይሔዳሉ እነርሱም እያንዳንዳቸው አራት ገጽ ሲኖራቸው ሳያርፉና ሳይደክሙ የሚያመሰግኑ ናቸው" በማለት ጽፏል። ነብዩ ሕዝቅኤልም በምዕራፍ 1÷6-13 "ለእያንዳንዱ እንስሳትም የተለያዩ አራት ገጾች ነበሩት። ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር አራት ገጽ ካላቸው ኪሩቤል መካከል አንዱ ንስር መሆኑን ነው። ቅዱስ ራጉኤል ደግሞ የኪሩቤል አለቃቸው የጌትነቱ ዙፋን ጠባቂ በመሆኑ በዚህ ምክንያት እነርሱ ዙፋኑን ተሸካሚ እርሱ ደግሞ አጠገባቸው መቆሙ መንበሩን ጠባቂ በመሆኑ በዚህ አይነት የአገልግሎት ድርሻ አብረው ሊሳሉ ችለዋል።

ገዳማውያንን ከመንፈሳዊው ጠላት ጋር ሲዋጉ ኃይል፣ ጽንዕ ብርታት የሚሰጣቸው ቅዱስ ራጉኤል ነው፡፡ እኛም ገዳማቸውን በመደገፍ በዓታቸውን በማጽናት የበረታቸው ተሳታፊ እንሁን፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

27 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.