Logo
Getu Temesgen
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በእስራዔል ሮሽ ሐሻናህ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላለፉ
#ethiopia | ​በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በተከበረው የዕብራውያን አዲስ ዓመት መጀመሪያ “ሮሽ ሐሻናህ” በዓል ላይ የተገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ለተሰበሰቡት እንግዶችና ለመላው የእስራኤል ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው በንግግራቸው የሮሽ ሐሻናህ በዓል አመጣጥ ከኖህ ዘመን ጀምሮ እስከ ሙሴ የዘለቀ ጥንታዊ ታሪክ ያለው መሆኑን በማስታወስ የበዓሉ መከበር የጥንታዊ እምነትና ባህል መቀጠል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

​ይህ የዕብራውያን አዲስ ዓመት በዓል ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አዲስ ዓመት ለማከበር በጥቂት ቀናት ዋዜማ ላይ ባሉበት ወቅት መከበሩ ቀኑን የበለጠ ልዩና ትርጉም ያለው እንደሚያደርገው ያመለከቱት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እግዚአብሔር ለሁለቱም ሀገራት ዘላቂ ሰላምን፣ ፍቅርንና እድገትን እንዲሰጥ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

​በበዓሉ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና የረጅም ዘመን ወዳጅነት በማንሳት ይህንን የጠበቀ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ አያይዘውም መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ በማለት አዲሱ ዘመን የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆንላቸው ልባዊ ምኞታቸውን አስተላልፈዋ።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዚህ መርሃ ግብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መንፈሳዊና ባህላዊ ቁርኝት የበለጠ የጠነከረ መሆኑ ተመላክቷል ።

(የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ)

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.