Logo
Getu Temesgen
ተባባሪ ፕ/ር ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ(ዶ/ር) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመመረቃቸው ልዩ የደስታና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ
#ethiopia | በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ፣ የቦርድና የሴኔት አባላት ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ለደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተባባሪ ፕሮፌሰር ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር) ልዩ የደስታና የምስጋና መርሃ ግብር አካሄዱ።

ይህ ታላቅ መርሃ ግብር የተዘጋጀው ብፁዕነታቸው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው ሊበርቲ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት አመራር ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በከፍተኛ መዐርግ በማጠናቀቃቸው ምክንያት ነው።

​በበዓሉ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት መልአከ ኃይል አባ ጽጌ ደንግል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላላፊ ሲሆኑ ይህ ስኬት የአንድ ሰው የትምህርት ውጤት ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለሚመጣው ትውልድ የሚተላለፍ የታላቅ ተስፋና የእውቀት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የብፁዕነታቸውን የትምህርትና የአገልግሎት ጉዞ የሚያስረዳ "ፍኖተ ሕይወት" መጽሔት፣ "ከአሜሪካ እስከ ጂንካ" የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እና የዩኒቨርሲቲውን ታሪካዊ እድገት የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ ለታዳሚዎች ቀርቧል።

​የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል ግርማ በበኩላቸው የብፁዕነታቸውን የመመረቂያ ጥናት ዳሰሳ ያቀረቡ ሲሆን ጥናቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዐውድ ውስጥ አገልጋይ መሪነትን፣ የሥራ ተነሣሽነትን እና መንፈሳዊነትን ያቀናጀና የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ ተልዕኮ መሰረት ያደረገ ትልቅ የምርምር አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

​ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በተደረገላቸው አቀባበል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ የተገኘው ውጤት የቤተክርስቲያኒቱ የጋራ ስኬት መሆኑን በመጥቀስ ለተማሪዎች ውጤታማነት ግልጽ ዓላማ፣ ጽናት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ ትክክለኛ የጥናት ስልትና የማኅበራዊ ሕይወት ድጋፍ ወሳኝ መሆናቸውን አበክረው ተናግረዋል።

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስም ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት፣ ብፁዕነታቸው ሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ዓለም አቀፍ እውቀት ጋር አጣጥመው በመያዝ ዘመኑን የዋጀ እረኝነትን በተግባር ያሳዩ ታላቅ አርአያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኹነቱ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

(EOTC -TV)

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.