Logo
EBC
የአፍሪካን ትክክለኛ ስፋት የሚያሳየው አዲሱ ካርታ መፅደቁ ታሪካዊ ድል ነው - ማህሙድ አሊ የሱፍ
****************

የአፍሪካን ትክክለኛ እና እውነተኛ ስፋቷን የሚያሳየው አዲሱ የዓለም ካርታ መፅደቁ ታሪካዊ ድል መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ ገለፁ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካን እና የሌሎችን የዓለም ክፍሎች እውነተኛና ትክክለኛ ስፋት የሚያሳይ አዲስ የካርታ አሰራር ውሳኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በመፅደቁ ለመላው አፍሪካውያን የአንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ውሳኔው በቶጎ አቅራቢነት እና በአፍሪካ ቡድን ስም የቀረበ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሊቀመንበሩ ለዚሁ ስኬት የቶጎ ሪፐብሊክ ያሳየችውን አመራር እና የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ፎሬ እሶዚምና ኛሲንግቤ ቁርጠኝነት ያደነቁ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እና በኒውዮርክ የሚገኘው የአፍሪካ ቡድን ላሳዩት አንድነትና ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

በ16ኛው ክፍለ ዘመን ለባህር ጉዞ ማመቻቻ ተብሎ የተሰራው የሜርኬተር (Mercator) ካርታ፤ የአፍሪካን አህጉር ትክክለኛ ስፋት እጅግ አሳንሶ እንደሚያሳይ ያብራሩት ማህሙድ አሊ የሱፍ፤ የአዲሱ ውሳኔ መጽደቅ ይህንን ታሪካዊ ስህተት የሚያርም ትልቅ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።

አህጉሪቱን በሳይንሳዊና ተጨባጭ እውነታዎች ላይ ተመስርቶ ማሳወቅ ወሳኝ መሆኑን ያሰመሩበት ሊቀመንበሩ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የትምህርት ስርአቶች፣ አታሚዎች እና የዲጂታል አቅራቢዎች አዲሱንና ትክክለኛውን የካርታ ምስል ደረጃ በደረጃ ስራ ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከቶጎ፣ ከአባል ሀገራት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የውሳኔ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.