Logo
EBC
ኢትዮጵያውያን መከሩ፤ ኢትዮጵያም አሸነፈች! - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
***********

ኢትዮጵያ የኃይልና የግጭት ፖለቲካን በቃ በማለት ልዩነቶቿን በሰለጠነ የምክክር መድረክ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር በአዲስ መሠረት ላይ የጣለ ታሪካዊ ድል ሆኗል ሲል የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ዛሬ የተከናወነውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተመለከተ በፌስቡክ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ባጋራው መልዕክት፥ በኢትዮጵያ የጥቂት ልሂቃን የጥቅም ድርድር የነበሩ የዝግ በር ልማዶችን የቀየረና፣ ሰፊውን ሕዝብ የውሳኔው ቀጥተኛ ባለቤት ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ብሏል።

በዚህም ዜጎች ለዘመናት ያጋጠሟቸውን ታሪካዊ ስብራቶች፣ ጥልቅ አለመግባባቶችና የሐሳብ ልዩነቶች በኃይል ሳይሆን በመደማመጥና በጋራ ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ በተግባር አስመስክረዋልም ብሏል አገልግሎቱ።

በሁሉም ክልልሎች ከቀበሌ እስከ ፌደራል በተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ/ አርብቶ አደሮች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የብሔር-ብሔረሰቦችና እምነቶች ተወካዮች እንዲሁም ምሁራንና ሊቃውንት በስምንት አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት ሁሉን አቀፍ ውይይት የ130 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ ማድመጣቸውን ገልጿል።

በዚህም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በንግግር ብቻ መሆኑን ፍጹም አካታች በሆነ አርዓያነት አረጋግጠዋል ነው ያለው።

አገልግሎቱ አክሎ እንዳለው፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከባንዳዎቸ ጋር ተጣምረው በዲጂታል ሚዲያ የሐሰት መረጃና ውዥንብር ለመፍጠር ቢሞክሩም፣ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን በጥብቅ ዲስፕሊን በመመራት በጽናት አስከብሯል።

ከ54 በላይ የሚዲያ ተቋማትና 461 ጋዜጠኞች ሂደቱን በቀጥታ ሽፋን በመስጠት ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መቻላቸውን ጠቅሷል።

በልጆቿ ፍጹማዊ ፅናት በተከናወነው በዚህ ታሪካዊ ክንውን፣ ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በገዛ እጇ መወሰን እንደምትችል በተግባር አሳይታለች፤ ኢትዮጵያውያን መከሩ፣ ኢትዮጵያም አሸነፈች ብሏል የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
#ethiopia #nationaldialogue #peacebuilding #historicconsensus #ethiopiawins #ebc

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.