Logo
EBC
የደቡብ ኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት ሞዴል፦ ወላይታ ሶዶ በአዲስ ገፅታ
*******************

የዓለም ህዝቦች የባህል ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓል በመስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ይከበራል።

ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በርካታ እንግዶች በሚታደሙበት በዚህ ታላቅ በዓል አቀባበል ለማድረግ በወላይታ ሶዶ ከተማ የተለያዩ ቅድመ-ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። የዚሁ ዝግጅት አካል የሆነው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ስራ ለአይን ማራኪና ለቀልብ ሳቢ ሆኖ ከተማዋን አስውቧታል።

በከተማዋ በየደረጃው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ስራዎችን አስተሳስሮ የያዘ ነው። ይህም የመንገድ ጥገናን፣ የዘመናዊ መንገድ ማብራት ዝርጋታን፣ የውሃና የኤሌክትሪክ መስመሮችን፣ እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃዎችን አቀናጅቶ በሁለቱም የመንገድ ዳርቻዎች የማዋሃድ ስራን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የመናፈሻ ስፍራዎች፣ የህዝብ መገልገያ ካፌዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተካተውበታል።

ባህልን ከታሪክ ጋር አስተሳስሮ በሚከናወነው በዚህ ዙር የኮሪደር ልማት፣ ቀደም ሲል ለህዝባቸው ታላቅ ውለታ የዋሉ ጀግኖች መታሰቢያ ሐውልቶች እየተገነቡ ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የካዎ ጦና እና የፍሬው አልታዬ መታሰቢያ ሐውልቶች ለከተማዋ ተጨማሪ ሞገስና ውበት ሆኗታል።

በሌላ በኩል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ በተጀመረው ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ መሰረት የ"ሶዶ መሶብ አንድ ማዕከል" ግንባታም በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ፅዱና ተመራጭ የማድረግ ሀገራዊ እንቅስቃሴ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በክልሉ በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት ለከተሞች ልማትና ዝግጅት ልዩ ዕድል ፈጥረዋል።

በዚህም መሰረት ቀን ቀጠሮ ለተቆረጠለትና በመስከረም 10/2019 ዓ.ም ለሚከበረው የጊፋታ በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማ ልዩና ደማቅ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በትዕግስቱ ቡቼ

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.