Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ዩኤን ዋች ‹‹የኤርትራ በሰብአዊ ምክር ቤት መመረጥ አስከፊ ቀልድ ነው›› አለ፡፡ መቀመጫውን በጄኔቭ ያደረገውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አሰራር የሚከታተለው ‹ዩኤን ዋች›› ዛሬ ባወጣው መግለጫ ኤርትራ በተመድ ሰብአዊ መብት ምክር ቤት ውስጥ የማህበራዊ መድረክ ሊቀመንበር ሆና መመረጧን አጥብቆ እንደሚቃወም ገለፀ፡፡ ውሳኔውንም ‹‹በአለም ላይ ካሉ ጨቋኝ መንግስታት አንዱን የሰብአዊ መብትን ለማሳደግ በሚጥር አካል ውስጥ ሀላፊነት መስጠር አስከፊ ቀልድ ነው›› ብሎታል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሂሌል ኑየር ሲናገሩ ‹‹ኤርትራ በወታደራዊ ሀይል የምትተዳደር የአንድ ፓርቲ አምባገነን አገር ስትሆን በፍሪደም ሀውስ ከ100 ነጥብ ውስጥ 3 ያገኘች ናት፡፡ ይህ ማለት የሰብአዊ መብት ሪከርዷ እጅግ የከፋ ነው›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹የኤርትራ መንግስት እ.ኤ.አ ከ1993 አገሪቱ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ምንም አይነት ብሄራዊ ምርጫ አላካሄደም፡፡

እንደባርነት የሚቆጠር የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን ያስፈፅማል፡፡ የሚተቹትንና ጋዜጠኞችን ለአስርት አመታት ያለምንም ክስ ያስራል፡፡ የፖለቲካ እስረኞችንና የሀይማኖት አባቶችን ያሰቃያል፡፡ ይህ የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ ተብሎ የሚጠራው መንግስት ከሰብአዊ መብቶች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ የኤርትራን መንግስት እዚህ ወንበር ላይ ማስቀመጥ እጅግ መጥፎ ቀልድ ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የራሱን ደንቦች ማክበር እያቃተው ለመሆኑ ይህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቀሱት ዳይሬክተሩ አስከትለውም ‹‹በሰብአዊ መብት ምክር ቤቱ ውስጥ የተወከሉትን ሁለንተናዊ መብቶች እንደሚከላከሉ የሚናገሩ መንግስታት በተለይም እንደፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ብራዚልና ስዊዘርላንድ የመሳሰሉ የምክር ቤቱ አባላት ይህንን የኤርትራን ሹመት አውግዘው መግለጫ እንዲያወጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ይህ አፀያፊ ሹመት እንዲቀለበስ በማድረግም የኤርትራ መንግስት በሰብአዊ መብት ረገድ ምንም እውቅና እንዳይሰጠው ማድረግ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ በማጠቃለያቸውም ‹‹ይህ ሹመት አምባገነንነትን የሚሸልምና የሰብአዊ መብት ምክር ቤቱ የተነሳለትን አላማ የሚክድ ነው፡፡ አለም ይህንን እየተመለከተ ነው፡፡ ዝም የሚሉ ዲሞክራሲዎች ለዚህ አሳፋሪ ውሳኔ ሀላፊነቱን ይወስዳሉ›› በማለት መግለፃቸውን ከመግለጫው ላይ ተመልክተናል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.