Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው አርሰናል፣ በአየርላንዷ ዱብሊን ከተማ ከስፔኑ ሪያል ቤቲስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያልተጠበቀ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ የተጫዋቾቹ ስሜት በእጅጉ መጎዳቱን አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ገለጹ።

መድፈኞቹ ባልተለመደ ሁኔታ የመከላከያ ክፍላቸው ክፉኛ ተዳክሞ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ሶስት ግቦችን ለማስተናገድ ተገደዋል። ምንም እንኳን ቤቲሶች የኳስ ቁጥጥሩን ለአርሰናል አሳልፈው ቢሰጡም፣ እጅግ አደገኛ በሆኑ ሙከራዎች እና ዒላማቸውን በጠበቁ ኳሶች የአርቴታን ልጆች ብልጫ ወስደውባቸዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ መጥፎ አቋም በኋላ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ስለነበረው ድባብ የተጠየቁት አርቴታ "በጣም ተበሳጭተዋል፣ ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፉት። በንዴት ጦፈዋል፤ ግን ይሄ ጥሩ ነው። እኛም የምንፈልገው ይሄንን ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አርቴታ አክለውም "ዋናው ነገር ማሸነፍ ነበር፣ ግን አልቻልንም፤ ስለዚህ በውጤቱ ማዘናችን አይቀርም። ሆኖም መጥፎ ውጤት ማምጣት ለቀጣይ የተሻለ ስራ የድል ረሃብን ስለሚፈጥር አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

የዓለም ዋንጫ ተሳትፎን ተከትሎ ዴክላን ራይስ፣ ኤቤሬቺ ኤዜ፣ ኖኒ ማዱኤኬ እና ቡካዮ ሳካ አሁንም ስብስቡን አልተቀላቀሉም። የስፔን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ሚኬል ሜሪኖ፣ ዴቪድ ራያ እና ማርቲን ዙቢሜንዲም እንዲሁ አልተመለሱም። አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ግን ከኖርዌይ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎው መልስ ግላዊ ልምምድ ጀምሯል።

ይሁን እንጂ አርሰናል እነዚህ ቁልፍ ተጫዋቾች ባይኖሩትም በቋሚ አሰላለፉ አራት ዓለም አቀፍ ተከላካዮችን፣ እንዲሁም ኢታን ኑዋኔሪ፣ ካይ ሃቨርትዝ፣ አዲሱ ፈራሚ ክሪስቶስ ዞሊስ እና ማክስ ዶውማንን በአማካይ ስፍራ፣ ቪክቶር ጊዮከረስን ደግሞ በአጥቂ መስመር አሰልፎ ነበር።

ባለፈው ሳምንት ጂሮናን 4-1 ባሸነፈበት አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገባው አርሰናል፣ በጨዋታው መባቻ ጊዮከረስ ያገኘውን ግሩም አጋጣሚ የቤቲሱ ግብ ጠባቂ አልቫሮ ቫሌስ በእግሩ መልሶበታል። ሆኖም በ9ኛው ደቂቃ ላይ አርሰናሎች ጠንካራ ከሆኑበት የማዕዘን ምት ቤቲሶች ቀዳሚውን ግብ አግኝተዋል። ተቀያሪው ግብ ጠባቂ ኬፓ አሪዛባላጋ በፓብሎ ፎርናልስ የተመታውን ኳስ በአግባቡ ባለማንበቡ፣ ሮድሪጎ ሪኬልሜ ያለምንም ከልካይ ኳሷን መረብ ላይ አሳርፏል።

በአማካይ ስፍራ የተሰለፈው ወጣቱ ማይልስ ሉዊስ-ስኬሊ ከሌሎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን፣ ሪካርዶ ካላፊዮሪ ወደ ፊት በሚሄድበት ጊዜ ቦታውን እየሸፈነ ድንቅ ስራ ሰርቷል። የግሪኩ ክንፍ ተጫዋች ዞሊስ የግብ ጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ አቻ የሚያደርግበትን ኳስ ቢያገኝም ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የተመለሰው ሪያል ቤቲስ፣ በአርሰናል ስህተቶች ላይ በሚገባ ተጫውቷል። በ26ኛው ደቂቃ ኬፓ የሰራውን ደካማ የኳስ አወጣጥ ስህተት ተጠቅሞ ኔልሰን ዴኦሳ ከ25 ያርድ ርቀት ላይ አስደናቂ ግብ አስቆጥሯል። በ32ኛው ደቂቃ ዞሊስ ያሻገረውን ኳስ ፒዬሮ ሂንካፒ በጭንቅላቱ በመግጨት ለአርሰናል አንድ ግብ ቢመልስም፣ በ43ኛው ደቂቃ ላይ ካይ ሃቨርትዝ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ፓብሎ ፎርናልስ የቤቲስን ሶስተኛ ግብ ከመረብ አዋህዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ አርቴታ ጋብሪኤል ማርቲኔሊን እና ጋብሪኤል ማጋልሃስን ጨምሮ ሰባት ተጫዋቾችን ቀይረው አስገብተዋል። የ16 ዓመቱ ተከላካይ ማርሊ ሳልሞን እና የ19 ዓመቱ ሉዊ ኮፕሊም የመሰለፍ እድል ቢያገኙም፣ ኮፕሊ ገብቶ በሰባት ደቂቃ ውስጥ በደረሰበት የጉልበት ጉዳት ለመውጣት ተገዷል። በቅያሪዎች ብዛት የጨዋታው ምት የቀዘቀዘ ሲሆን፣ ጋብሪኤል ጄሱስ የተሻለ ሙከራ ቢያደርግም፣ አርቴታ በሜዳው ዳርቻ በብስጭት ሲንጎራደዱ ታይተዋል፤ መድፈኞቹም ያጡትን ክፍተት ማጥበብ ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.