Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት) አዲሱ የሱፐርማን ፊልም በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ የጄምስ ገን የዲሲ ኮሚክስ ዩኒቨርስ የመጀመሪያው ትልቅ የሲኒማ ፊልም በመሆኑ የተለየ ትኩረት ስቦለታል። በዚህ ፊልም ላይ ከተለመዱት የሱፐርማን ገጸ-ባህሪያት በተጨማሪ ሚስተር ቴሪፊክ የተባለው ገጸ-ባህሪ ተካቷል። ይህ ገጸ-ባህሪ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም ያለው፣ ምጡቅ መሃንዲስ እና ሳይንቲስት፣ እንዲሁም በሰው ለሰው ውጊያ የተካነ ነው። ሚስተር ቴሪፊክን ወክሎ የሚጫወተው ኤዲ ጋቴጊ፣ ለረጅም ጊዜ በፊልም እና ቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆየ ቢሆንም፣ የፊቱ ገጽታ እንጂ ስሙ በብዙዎች ዘንድ በደንብ አይታወቅም።

የትውልደ ኬንያዊው አሜሪካዊ ተዋናይ የፊልም ህይወት በ2006 በ'ክራንክ' ፊልም ላይ በታክሲ ሹፌርነት የጀመረ ሲሆን፣ በመቀጠልም በ'ሀውስ'፣ 'ሲኤስአይ፡ ማያሚ' እና የመሳሰሉት የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል። 'ሱፐርማን' ለጋቴጊ የመጀመሪያው የሱፐርሂሮ ፊልም አይደለም። ከዚህ ቀደም በ2011 በወጣው 'ኤክስ-ሜን፡ ፈርስት ክላስ' ፊልም ላይ 'ዳርዊን' የተባለውን ማናቸውንም አደጋዎች ተቋቁሞ በህይወት መቆየት የሚችል የ'ማርቨል' ገጸ-ባህሪን ወክሎ ከታዋቂ ተዋንያን ጋር ተጫውቷል።

ጋቴጊ ከ'ኤክስ-ሜን' በፊት በታዋቂው የ'ትዋይላይት' ፊልም ላይ ሎረንት የተባለውን ቫምፓየር ሆኖ በመተወን ይታወቃል። ምንም እንኳን ገጸ-ባህሪው በፊልሙ ላይ ቢገደልም፣ ቫምፓየር ሆኖ የመተወን የረጅም ጊዜ ህልም እንደነበረው ተዋናዩ ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ በታዋቂው የ'ብላክሊስት' ተከታታይ ፊልም ላይ፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀል የፈጸመውን እና የሲአይኤ ሰላይ የነበረውን ማቲያስ ሰለሞን የተባለ አደገኛ ገጸ-ባህሪን ወክሎ ከ20 በላይ ክፍሎች ላይ ተሳትፏል።

ተዋናዩ በ2016 በታየው 'ስታርትአፕ' ላይም ሮናልድ ዴሲ በተባለ ዋና ገጸ-ባህሪነት የተጫወተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአፕል ቲቪ+ (Apple TV+) 'ፎር ኦል ማንካይንድ'በተሰኘው የሳይንስ ልብወለድ ተከታታይ ፊልም ላይ ዴቭ አዬሳ የተባለውን ታዋቂ መሃንዲስ፣ የኩባንያ መስራች እና ነጋዴ ወክሎ በመተወን ላይ ይገኛል። አሁን ደግሞ በ'ሱፐርማን' ፊልም ላይ በሚጫወተው የሚስተር ቴሪፊክ ሚና በድጋሚ የብዙዎችን ትኩረት ወደ ራሱ እየሳበ ይገኛል።

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.