ዓለምን ዳግም ወደ ስጋት የከተተው የቴህራን እና ዋሽንግተን ወታደራዊ ግጭት
**********************
ባለፈው ወር በፓኪስታን አጋዥነት የተደረሰው የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ተከትሎ፣ በሁለቱ ኃይላት መካከል ለቀናት የቀጠለው ጥቃት የቀጣናውን የጸጥታና የዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ መስመር ከባድ ሥጋት ላይ ጥሎታል።
አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ወደ መጣስ እና የኒውክሌር ተቋማትን ወደ ማጥቃት የተሸጋገረው ይህ አደገኛ ምዕራፍ፣ መላውን ዓለም ወደማይወጣበት ሁለንተናዊ ቀውስ ሊከተው የሚችል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የግጭቱ መነሻ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) ይፋ ባደረገው መግለጫ መሠረት፣ በዮርዳኖስ በሚገኝ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ በተሰነዘረ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውንና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ተከትሎ የተከሰተ ነው።
ዋሽንግተን ለዚህ አጸፋዊ ምላሽ ይሆን ዘንድ በደቡባዊና ደቡብ ምዕራብ ኢራን በሚገኘው የዳርክሆቨይን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ቦታ ላይ ሳይቀር ያነጣጠረ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች።
ፔንታገን ጥቃቱን በቀጥታ ከማረጋገጥም ሆነ ከመካድ የተቆጠበ ቢሆንም፣ "አሜሪካ ወታደሮቿን ከጥቃት ለመከላከልና የኢራንን የማጥቃት አቅም ለማዳከም ማንኛውንም እርምጃ ትወስዳለች" ሲል ድርጊቱን በተዘዋዋሪ ተከላክሏል፤ ጥቃቶቹም በዋናነት የኢራንን ወታደራዊ የሎጅስቲክስ መሠረተ-ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ መሆቸውን ትሟገታለች።
ይሁን እንጂ የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ጥቃቱን "የሀገሪቱን የሳይንስ ዕድገትና ነጻነት ለማደናቀፍ የታለመ አረመኔያዊ የሽብር ድርጊት" ሲል በጽኑ ኮንኖታል።
ቴህራን ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የደኅንነት ጥበቃ ሥርዓት ተገዢና ሰላማዊ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ መጣሷን አስታውቃለች።
በአሜሪካ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ እስካሁን በኢራን ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውንና ከ500 በላይ መቁሰላቸውን የገለጸው የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር፣ በርካታ ድልድዮችና ሲቪል መሠረተ-ልማቶች መውደማቸውን አረጋግጧል።
ለአሜሪካ ጥቃት የኢራን ወታደራዊ ምላሽ ፈጣንና መጠነ-ሰፊ የነበረ ሲሆን፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል "ናስር-2" የተሰኘውንና 20ኛ ምዕራፍ ላይ የደረሰውን የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን፣ የኢራን መደበኛ ጦር በበኩሉ "ሳዕቃ" የተሰኘውን 15ኛ ምዕራፍ የጥቃት ዘመቻ አካሂዷል።
በጥቃቶቹ በኩዌት የሚገኘው አሊ አል-ሳሌም የአየር ኃይል ሰፈር፣ ካምፕ አሪፍጃን፣ ካምፕ አዳይሪ እና ሚና አብዱላህ የተሰኘው የሎጂስቲክስ ማዕከል በከባድ ሁኔታ ተመተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በባህሬን የሚገኘው የአሜሪካ አምስተኛ ፍሊት ዋና መሥሪያ ቤት እና በዮርዳኖስ በሚገኘው አል-አዝራቅ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ምንም እንኳ የአሜሪካ እና የባሕረ-ሰላጤው አገራት መከላከያ ተቋማት አብዛኞቹን የኢራን ሚሳኤሎችና ድሮኖች ማክሸፋቸውን በይፋ ቢገልጹም፣ የወጡ የሳተላይት ምስሎች ግን የተለየ እውነታ እያሳዩ ነው።
የዋሽንግተን ፖስት የምርመራ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በክልሉ በሚገኙ 15 የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ውስጥ የራዳር ሥርዓቶች፣ የፓትሪዮት መከላከያ መሣሪያዎች እና የመጋዘን ተቋማትን ጨምሮ 228 መዋቅሮች በከፊልም ሆነ በሙሉ መውደማቸውን አረጋግጧል።
ይህ ወታደራዊ መካረር በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ መናወጥን አስከትሏል። የኢራንን ይፋዊ አቤቱታ ተከትሎ፣ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባወጡት መግለጫ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች ቁጥር 444 እና 533 መሠረት፣ በሰላማዊ የኒውክሌር ተቋማት ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ መሆኑን አስታውሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው፣ የኒውክሌር ተቋማትን ኢላማ ማድረግ የቀጣናውን ውጥረት ወደማይመለስ አደገኛ አደጋ ሊቀይረው እንደሚችል አስጠንቅቀው፣ የጸጥታው ምክር ቤት በአስቸኳይ እንዲመክርና ሁለቱም ወገኖች ራስን የመግታት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
"የኒውክሌር መሠረተ-ልማቶችን ማጥቃት ቀጣናውን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ወደማይወጣበት ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ የሚከት አደገኛ ድርጊት ነው" የሚለው የሰላም ጥሪ መግለጫ የሁኔታውን አሳሳቢነት በግልጽ ያሳያል።
በፖለቲካው ረገድ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የቃላት መለዋወጥ ይበልጥ ጠንክሯል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን በኩዌትና ባህሬን ላሉት የጦር ሰፈሮቿ ተጨማሪ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን በፍጥነት ለማስፈር እያቀደች መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ኢራን የኒውክሌር ታጣቂ እንድትሆን ፈጽሞ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ የኢራን መንፈሣዊ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና የፓርላማው አፈ-ጉባኤ መሀመድ ባቄር ቃሊባፍ፣ ዋሽንግተን ስምምነቱን በተጠቀሰው መሠረት ደጋግማ መጣሷ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፊርማ ፍጹም ዋጋ ቢስ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል። የሀገሪቱን ደኅንነት ለማረጋገጥ መላው የኢራን ሕዝብ ቅዱስ ያሉት "አንድነት" እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዋሽንግተን በኢራን ወደቦች ላይ የባሕር እገዳ ለመጣል መሞከሯን ተከትሎ፣ ቴህራን በበኩሏ የዓለም የነዳጅ ንግድ ወሳኝ የደም ሥር የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆኑን አውጃለች።
ይህንን የባሕረ-ሰላጤው መዘጋት ተከትሎ፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ (Brent Crude) በአንድ ጀምበር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ተንታኞች ውጥረቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በተለይ በእስያ እና በአውሮፓ አገራት ላይ ከባድ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ ግሽበት ሊከሰት እንደሚችልና የንግድ መርከቦች ረጅም ርቀት ወደሚጠይቀው የአፍሪካ አቅጣጫ መስመራቸውን ለመቀየር እየተገደዱ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።
ፍጥጫው ወታደራዊ ጡንቻን ከማሳየት አልፎ የዓለምን መደበኛ የኢኮኖሚና የጸጥታ መዋቅር የቀየረ ታሪካዊ ቀውስ ሆኗል።
በሰለሞን ገዳ

3 months ago