Logo
EBC
"ሁላችንም መሣሪያ አስቀምጠን በአንድነት አሸናፊ የምንሆንበት ዕድል ተፈጥሯል" - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
***********************

እየተከናወነ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ያለ ምንም የጦር መሣሪያና ጠመንጃ፣ ወገኖች በሐሳብ ብቻ እየተነጋገሩና እየተደማመጡ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ታሪካዊ መድረክ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ከኢቲቪ ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሂደቱ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመው፣ በሂደቱ ስኬታማነት ላይ ሙሉ እምነትና እርግጠኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሐምሌ 8 በሚጀመረው ታሪካዊ ጉባኤ የሚመካከሩ ተሳታፊዎች ከየወረዳው፣ ከክልሎች፣ ከፌደራል እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ የኢትዮጵያውያን እንግዶች በአሁኑ ወቅት ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ መግባት መጀመራቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

እንግዶቹን በፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እንዲሁም በተለያዩ ሆቴሎች የመቀበልና የማስተናገድ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ይህ ጉባኤ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ ከ4,000 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጥምረት የሚሳተፉበት በመሆኑ እጅግ ሁሉን አቀፍና አካታች ያደርገዋል ብለዋል።

ታላቁ ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት በርካታ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ በኮንቬንሽን ሴንተርና በዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሾች በሚኖራቸው ቆይታ የሥነ-ምግባር ደንቦችን እንዲረዱ፣ የምክክር ሂደቱን ዝርዝር መመሪያዎች እንዲገነዘቡ እና ከአማካካሪዎች ጋር የቅድመ-ውይይት ትውውቅና ዝግጅት እንዲያከናውኑ እንደሚደረግ ዋና ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመላው የሀገሪቱ ሕዝብ የተሰበሰቡ ከሁለት ሺህ በላይ አጀንዳዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ከእነዚህ ውስጥ መሠረታዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ስምንት ትልልቅ አጀንዳዎች በጥልቀት ተለይተው ለግምገማ ቀርበው መፅደቃቸውን ጠቁመዋል።

ተመካካሪዎቹ በ8 የተለያዩ ቦታዎች በየ500 ቡድን በመሆን በእነዚህ በጸደቁት አጀንዳዎች ላይ በሰፊው እንደሚመክሩም ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አክለውም፤ የምክክር ሂደት ጊዜና ትዕግሥት የሚወስድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥብቅ ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበው፤ ሂደቱ ሁሉንም ዜጋ ባሳተፈና ስልጣኔ በተሞላበት መንገድ መላው ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ እንደሚያደርግ ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።

በመሀመድ ፊጣሞ
#ebc #nationaldialogue #inclusiveethiopia #dialogueforpeace #nationalconsultation

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.