Logo
Getu Temesgen
♦️1:45 ደቂቃ በቶሮንቶ ሠማይ ስር

♦️FIFA እና Destination Toronto በጋራ የሠጡኝ ወርቃማ የጉብኝት ዕድል(ክፍል አንድ)

♦️ቶሮንቶን ከሜዳ ውጪ(Off the Pitch)

የ2026ቱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮኛል FIFA እና Destination Toronto ለአለም ዋንጫ ዘገባ ከመጡ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኞች ዛሬ የጉብኝት ዕድል ሠጥተውናል፤እኔም ይሄን ዕድል ካገኙት ጋዜጠኞች ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ሆኜ ቶሮንቶን ከእግር እስከራሷ የማየት ዕድል አግኝቻለሁ ከ1:45 ደቂቃ በላይ በዘለቀው የጉብኝት መርሃ ግብር የማውቃት የሚመስለኝ ነገር እንደማላውቃት የተረዳሁበትን አስገራሚ ጉብኝት አድርጌ በግርምት እጄን አፌ ላይ ጭኜ ተመልሻለሁ።ታሪክን፣ጥንታዊነትንና ዘመናዊነትን በውስጧ ሸሽጋ የያዘችው የኢኮኖሚ፣የቢዝነስ ከተማና ከ170+ አገሮች የመጡ ሰዎች የሚኖሩባት ባህላዊውን ከዘመናዊነት ጋር አጣምራ የያዘች ተወዳጅ ከተማ ናት።

በአንድ ጎዳና ላይ እየተራመዱ ብዙ ቋንቋዎችን ከሠሙ በትክክልም እርስዎ ያሉት ቶሮንቶ ነው፤ምክንያቱ ደግሞ ከ170 በላይ ሀገሮች የሚኖሩባት ብቻ ሳይሆን የተለየ ቋንቋ የሚነገርባት ዓለምን በአንድ ቦታ ሠብስባ የያዘች ከተማ ናትና።

በምሽት የካናዳ ምልክት ተደርጎ ከሚወሠደው፣ቶሮንቶን ልዩ ውበትና ድምቀት የሚያላብሳት CN Tower በሚፈልቀው ብርሃን፣በLake Ontario የባህር ዳርቻ ከወዳጅ ወይም ከፍቅረኛ ጋር የፍቅር ማር የሚቆረጥባት ከአለማችን ለኑሮ ምቹና ሠላማዊ ተብለው ከሚጠሩ ሀገሮች አንዷ፣ በዓመት ከ25–30 ሚሊዮን፣በበጋ ወቅት ደግሞ ከ150,000 በላይ ቱሪስቶች በቀን የምትጎበኘው የቱሪስቶች መዳረሻ የሆነችው ቶሮንቶን በToronto Double-Decker አውቶብስ አናት ላይ ተቀምጬ ታዘብኩትን የዛሬ የ1:45 ደቂቃ ጉብኝቴን በወፍ በረር ላስቃኛችሁ።

የተሳፈርንበትን Double-Decke Bus የሚዘውረው የህይወቱን ግማሽ ክፍል ለካናዳ የገበረው አቶ ፍቅሩ ብርሃኔ መሆኑ በጉብኝቴ የቤተሠብነት ስሜት እንዲሠማኝ ያደረገ ሲሆን በጣፍጭ አንደበቱ ታሪካዊ ቦታዎች የፍትፍት ያህል ፈትፍቶ ሲያጎርሠን የነበረውን አስጎብኚያችንን MASHAALን ከልብ ላመሠግነው ወደድኩ፤በቅድሚያ የጉብኝታችን መነሻ ስለነበረው

♦️University of Toronto

ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶሮንቶ ዕድሜ ጠገብ ነው፤የኛውን የቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአሁኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ123 ዓመት ዬበልጠዋል፤የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ76 ዓመት አዛውንት ሲሆን ዕድሜ ጠገቡ University of Toronto ደግሞ የ199 ዓመት አረጋዊ ነው፤እንደ አስጎብኚያችን MASHAALከ102 በላይ ተማሪዎችን እቅፍ ድግፍ አድርጎ በውስጡ ይዟል፤ዩኒቨርስቲውን ከአለማችን የተለየ የሚያደርገው ደግሞ ከ175 የዓለማችን ሀገሮች የመጡ ተማሪዎች መዳረሻ ብቻ ሳይሆን በባችለር፣በማስተርስና በፒኤችዲ ፕሮግራሞች በመታቀፍ ከህልማቸው የሚገናኙበት ትልቁ የዕውቀት ፋብሪካም ነው፤

በሚመደብለት ከ3.62 ቢሊየን የካናዳ ዶላር በካናዳ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ቀዳሚ የሆነው University of Toronto ካሉት ከ16ሺ የበለጡ ስታፎች ከ9ሺ በላዩ አስተዳደሩን የሚዘውሩ አመራሮች መሆናቸው ቶሮንቶን ያለ አዋዜ አጣጥሞ እንደበላት በቃሉ የሚሠጠው መረጃ ከሚያሳብቅበት አስጎብኚያችን MASHAAL መረዳትም ተችሏል።

ከዓለማችን ምርጥ 30 ዩኒቨርስቲዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት University of Toronto የአለምን በዕውቀታቸው እንዳሻቸው ከሚዘውሩ በዕውቀቱ የታጠቁ ሙሁራንን ከማፍራቱ በተጨማሪ የካናዳን ኢኮኖሚ በፍይናንስ ከሚያግዙ ተቋማት መካከልም አንዱ ነው፤በዚህም መሠረት ከ15 ቢሊየን የካናዳ ዶላር በላይ ወደ ካናዳ ፈሰስ መመድረጉ ይሄ ገቢዎች ነው?ወይስ ኢትዮ ቴሌኮም የሚል ጥያቄ ማስመዘዙ አልቀረም"

♦️TTC የቶሮንቶ ከተማ የልብ ምት

Toronto Transit Cooperation በምህፃረ ቃል TTC የደም ስር ወይም የከተማዋ የልብ ምት ቢባል ቃሉ አልተጋነነም፤በተለይም ለToronto እና አካባቢው ያበረከተው ጥቅም ከመጓጓዣነትም በላይ የሕይወት አገልግሎት ነው። ከተማዋን የሚያንቀሳቅስ ደም መስመር ተደርጎም ይቆጠራል፤TTC የከተማው የደም ሥር ነው።በቀላል አማርኛ
እንደ ደም ሥሮች ደምን ወደ ሰውነት ክፍሎች እንደሚያደርሱ ሁሉ TTC ሰዎችን ወደ ሥራ፣ ወደ ትምህርት ቤት፣ ወደ ሆስፒታል፣ ወደ ገበያ እና ወደ መዝናኛ ቦታዎች በየቀኑ በማመላለስ ህይወት በቶሮንቶ የቀለለ እንዲሆን እንዳደረገ በጉብኝታችን ወቅት ተረድተናል።

በቅርቡ የወጣ ጥናት እንደሌለ ነገር ግን የ2025ትን ጥናት መነሻ አድርጎ እንደ ነገረን አስጎብኚያችን MASHAAL መረጃ ከሆነነ የቶሮንቶን ከተማ ከጫፍ ጫፍ ለማገናኘት ማልደው የሚሠማሩት የTTC በእኛ ሀገር አጠራር የካናዳ አንበሳ አውቶቢስ አገልግሎት ከ2000 በላይ ቀይና ነጭ አውቶቢሶችን 250 የሚጠጉ ነኤሌክትሪክ፣ከ200 በላይ ረዣዥም ባሶችን ቶሮንቶ ትጠቀማለች።

የTTC የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባይካድም ትራፊክን ይቀንሳል፣መኪና መግዛት፣ ነዳጅ መሙላት እና ፓርኪንግ መክፈል ከሚጠይቀው ወጪ ይልቅ ብዙ ጊዜ ይቀላል፤ሰዎች በቀላሉ ወደ ሥራ እና ወደ ንግድ ማዕከላት እንዲደርሱም ከማገዙም በላይ ለሁሉም ተደራሽ በመሆን በኩል መኪና የሌላቸው፣ ተማሪዎች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ከተማው እንዳያገላቸው ይልቅ እንዲጠቀሙበት ትልቅ ዕድል ይሠጣል።ይህ ነፃና የተመቻቸ የትራንስፖርት ፍሠት ያለ TTC የባቡር አገልግሎት የተሳለጠ ይሆን ነበር ብሎ ለስህተት ይዳርጋል።ምክንያቱም የTTC ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት በዓመት ወደ ከ180 ሚሊዮን በላይ በቀን ደግሞ በየቀኑ ከ 690,000 በላይ ወይም 1ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን ከአንደኛው የከተማው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ በማመላለስ የቶሮንቶ የጀርባ አጥንት መሆኑን ጉብኝቴ አሳይቶኛል።

♦️በቶሮንቶ ከ110 ካሬ ኪ.ሜ. በላይ የሚሸፍን የተፈጥሮ ሸለቆዎች ያለባት ከተማ

አብዛኛው ሠው ስለ ቶሮንቶ ሲያስብ ከፊቱ ቀድሞ የሚመጣበት ወይም የካናዳና የቶሮንቶ መለያ አድርጎ የሚወስደው CN Tower ን ነው፤ከትናንቱ የሚዲያ ጉብኝቴ የተረዳሁት ትልቁ ቁምነገር ግን ቶሮንቶን ከሌሎች ትልልቅ ከተሞች የሚለየው የRavine System (የተፈጥሮ ሸለቆዎች አውታረ መረብ) ያለበት ከተማ መሆኑ ነው እላለሁ።ከላይ ለማነሳት እንደሞከርኩት ብዙ ሰዎች ስለቶሮንቶ ሲያስቡ የመጀመሪያው የሚያስታውሱት CN Tower ን ነው፣ ነገር ግን የቶሮንቶ እውነተኛ ልዩነት በከተማው መሃል ውስጥ የሚያልፉ የተፈጥሮ ሸለቆዎች መኖራቸውን ስንቶቻችን እናውቃለን?በሚገርማችሁ ሁኔታ በከተማው ውስጥ በአጠቃላይ 110 ካሬ ኪ.ሜ. የሚሸፍን የሸለቆ ስርዓት አለ፤

ይህ ደግሞ የከተማውን 17% በላይ እንደሚሸፍን የአስጎብኚያችን መረጃ ይጠቁማል፤በዓለም ላይ ቀከተማ ውስጥ ካሉ የሸለቆ ስርዓቶች ትልቁ በመሆንም ቶሮንቶን ከፊት ያስቀምጣታል።ስለዚህ በቶሮንቶ አንድ ሰው በዳውንታውን ውስጥ ያሉ ቁመተ መለሎ ሠማይ ጠቀስ ፎቆች መካከል ሲሆን ከ10 ደቂቃ በኋላ በዱር ውስጥ እንዳለ ሊሰማው ቢችል አይፈረድበትም፤ይሄንን የታዘቡ ደግሞ ቶሮንቶን “city within a park” (በፓርክ ውስጥ ያለች ከተማ) ብለው እስከመግለፅ የተገደዱት።

ቶሮንቶ ሰማይን የሚነኩ ሕንፃዎችና የተፈጥሮ ዱር በአንድ ቦታ የሚገናኙባት ከተማ መሆኗ በእርግጥም የተለየች ከተማ የሚል ስያሜ እንዲሠጣት ያስገድዳል።።

የክፍል አንድ የወፍ በረር ጉብኝቴ ይሄንን ይመስላል፤በክፍል ሁለት ትዝብቴ ቀ1:45 ደቂቃ በፈጀው ጉብኝቴ የካናዳዊያን ምልክት ተደርጎ ስለሚወሠደው CN Tower፣ስለ ሮያል ኦንታሪዮ ሙዚየም፣ቶሮንቶንስላጥለቀለቁት ላይብረሪዎች፣የፍቅር ማር ስለሚቆረጥባትና የመዝናኛ ዋነኛ የልብ ምት ስለሆነችው Lake Ontario እና በካናዳ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣የጉብኝት ባሳችንን Double-Decke ከሚዘውረው ኢትዮጵያዊ ህይወትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የቃረምኩትን አካፍላችኋለሁ፤FIFA እና Destination Toronto በጋራ ይሄን ዕድል ስለሠጡኝ ከልብ አመሠግናለሁ🙏🙏...(ይቀጥላል)....

✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከከናዳ ቶሮንቶ

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.