Logo
FBC
ሰላም! እንደምን አደራችሁ?

ኢትዮጵያን ወደ አቪዬሽን ማዕከልነት…

የቢሾፍቱ አቡሴራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዓለምን ለማስተሳሰር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን ከአህጉራዊ የትራንዚት ማዕከልነት ወደ መላው ዓለም ስልታዊ መገናኛ ድልድይነት ያሸጋግራታል፡፡

ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የአቪዬሽን መናኸሪያ ከማድረግ ባለፈ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር ኩራት የሚሆኑ የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያረጋግጡ በረከቶችን ይዞ እየመጣ ነው፡፡

ለግዙፉ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦለት፣ በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያው ምዕራፍ የመሬት ማስተካከል ሥራዎች ቀንና ሌሊት በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑለት ይገኛል።

ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 12 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚደረግበት ሲሆን÷ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት ለቦታው መሬት ማስተካከል እና የዝግጅት ሥራዎች 610 ሚሊየን ዶላር ተመድቦ ሥራው በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
የመጀመሪያው ዙር የመሬት ዝግጅት ሥራ እንደተጠናቀቀ፣ ዋና ዋናዎቹ የግንባታ ተቋራጮች ወደ ስፍራው ገብተው ግንባታቸውን ይጀምራሉ። የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በፈረንጆቹ እስከ 2030 ድረስ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ግብ ተቀምጧል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ ግዙፍ አቅም ይኖረዋል። ይህም አሁን ካለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅም በ4 ነጥብ 4 እጥፍ ይበልጣል። አየውሮፕላን ማረፊያው አራት ዘመናዊ ማኮብኮቢያዎች እና በአንድ ጊዜ እስከ 270 አውሮፕላኖችን ማቆም የሚችል ስፍራም ይኖረዋል።

አቡሴራ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከባሕር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ቦሌ (2 ሺህ 334 ሜትር) በተሻለ ለአውሮፕላኖች መነሳትና ማረፍ እጅግ ምቹ የአየር ሁኔታን ይሰጣል።

የፕሮጀክቱ ዲዛይን በታዋቂው የለንደን ዘሃ ሃዲድ አርክቴክትስ የተሰራ ሲሆን÷ በውስጡ ዘመናዊ ሆቴሎችን፣ የገበያ ማዕከላትን፣ የንግድና የዕቃ መጋዘን (Cargo) ኮምፕሌክሶችን ያካትታል። አዲሱ አየር ማረፊያ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በፈጣን የኤክስፕረስ መንገድ እና በከፍተኛ ፍጥነት ተንቀሳቃሽ የባቡር መስመር እንደሚገናኝ ይጠበቃል፡፡

ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እድገት ለማሳለጥ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ዘላቂ ሞተር ይሆናል። ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ አበርክቶው ከፍተኛ ነው፡፡

በግንባታው ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ መሃንዲሶችንና ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ያለ ሲሆን÷ ሥራ ሲጀምር ደግሞ በአየር መንገዱ፣ በሆቴሎችና በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን በማስተናገድ ከትራንዚት፣ ከቀረጥ ነፃ ንግድ እና ከአየር መንገድ አገልግሎቶች የሚገኘውን የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል። የአካባቢው የዶሮ፣ የወተት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ለግዙፉ አውሮፕላን ማረፊያና ለሆቴሎቹ ምርቶቻቸውን በስፋት የሚያቀርቡበት ሰፊ የገበያ እድልም ይፈጥርላቸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በሀገር ውስጥ ምርት እድገት፣ በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና በውጪ ምንዛሪም ማሳደግን ያስችላል፡፡ ማረፊያው በሚሊየን የሚቆጠሩ መንገደኞችን እና በሚሊየን የሚቆጠር ቶን ጭነት ማስተናገዱ በራሱ ለሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ቀጥተኛ እና ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።

ምቹ፣ ፈጣን እና ዘመናዊ የአየር ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት መኖሩ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎችና ፋብሪካዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዋነኛ ማበረታቻ ይሆናል።

ከአገልግሎቶች፣ ከነዳጅ ሽያጭ፣ ከትራንዚት ሆቴሎች እና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ማዕከላት የሚገኘው ገቢ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት ይቀርፋል።

የወጪ ንግድ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እድገት በማሳለጥ ረገድም የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ አበባ፣ ፍራፍሬ፣ አትክልትና ስጋ ያሉ በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ የኢትዮጵያ እና የሌሎች ሀገራት ወጪ ምርቶች ሳይዘገዩ በጥራት ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የገበሬውንና የላኪውን ገቢ ያሳድጋል።

በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ እና በሀገሪቱ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያመርቷቸውን የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ እና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ ገበያዎች ለማጓጓዝ ምቹ የሎጂስቲክስ ሰንሰለት ይፈጥራል።የአህጉሪቱ የንግድና የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ዋና ማስተላለፊያ ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ተሰሚነት ያጠናክራል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ደግሞ ሌላኛው ትሩፋቱ ይሆናል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ከማረፊያነት ባለፈ ዘመናዊ ሆቴሎችን፣ የገበያ ማዕከላትን፣ የኤግዚቢሽን ማዕከላትንና የንግድ ህንጻዎችን የያዘ "የኤርፖርት ከተማ" ወይም አዲስ የኢኮኖሚ ከተማ ሆኖ ይገነባል።

አካባቢው ለቱሪዝም ምቹ በመሆኑም ዓለም አቀፍ ቱሪዝምን ይስባል፡፡ በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅሙ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ የትራንዚት መንገደኞች ቢያንስ ለጥቂት ቀናት በሀገሪቱ እንዲቆዩ እና የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲጎበኙ በር ይከፍታል።
የቱሪስቶች ቁጥር መጨመር በሀገር ውስጥ ያሉ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች እና የባህል ምርቶች አቅራቢዎች ገቢያቸው እንዲያድግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ያደርጋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሰው ኃይል ልማት ላይ የሚኖረው አንድምታም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው የሚገነባው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የኤክስሬይ፣ የደህንነት፣ የሮቦቲክስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በመሆኑ የሀገር ውስጥ መሃንዲሶች እና ባለሙያዎች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላል።ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የሚስፋፉት የአቪዬሽን ማሰልጠኛዎች እና የምርምር ማዕከላት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የእውቀት ማዕከል ያደርጓታል።

በሌላ መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያን ክልላዊ የልማት መናኸሪያ ያደርጋታል፡፡ ፕሮጀክቱ ቢሾፍቱን፣ ሞጆን፣ ዱከምንና አዲስ አበባን የሚያስተሳስር አዲስ የኢኮኖሚ ኮሪደር ይፈጥራል። ይህ ከተሞች፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የኃይል እና የመገናኛ መሠረተ ልማቶችን በጥራት እንዲያድጉ ያደርጋል።

ከዚህ ባለፈም ዓለም አቀፋዊ ትስስርን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የመጀመሪያው ሚና የዓለም አቀፍ አየር መንገዶች መዳረሻነት ነው፡፡ በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው በመሆኑ፣ ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከላቲን አሜሪካ የሚነሱ ተያያዥ በረራዎችን በአንድ ማዕከል ያስተናግዳል ፤ ይህም ግዙፍ የመንገደኞች ፍሰትን ይፈጥራል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አባል የሆነበት ስታር አሊያንስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች አቡሴራን ዋና የምስራቅ አፍሪካ መሸጋገሪያ መናኸሪያቸው ያደርጉታል። የአሊያንስ ማዕከልነታችንንም የምናረጋግጥበት ይሆናል፡፡

ሁለተኛው ሚና የግሎባል ደቡብ ዋነኛ ትስስር ድልድይን መፍጠር ነው፡፡ አዲሱ ማረፊያ አፍሪካን ከላቲን አሜሪካ፣ ከእስያ (በተለይም ከቻይና እና ህንድ) እና ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር በቀጥታና በአጭር ሰዓት የሚያገናኝ ዋነኛ መስመር ይሆናል። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ከዓለም ጋር አስተሳሰርን ማለት ነው፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተፈፃሚነት ለማፋጠን ሰዎችንና የንግድ ዕቃዎችን ከአህጉሪቱ ጥግ እስከ ዓለም ጫፍ በፈጣን የሎጂስቲክስ ሰንሰለት ያገናኛል። ለአህጉር አቀፍ ንግድ መነቃቃት አበርክቶው ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ሦስተኛው የዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ማዕከልነታችንን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሚገነባው ግዙፍና ዘመናዊ የካርጎ ተርሚናል የዓለም የንግድ ዕቃዎች እና የህክምና አቅርቦቶች ከአምራች ሀገራት ተነስተው ወደ ተጠቃሚዎች የሚሰራጩበት ዋነኛ የአየር ሎጂስቲክስ ማዕከል እንዲሆን ያደርገዋል። እንደ አበባ፣ ፍራፍሬ እና ስጋ ያሉ የኢትዮጵያና የጎረቤት ሀገራት ምርቶች ሳይበላሹ በጥራትና በከፍተኛ ፍጥነት ወደ መላው ዓለም ገበያ እንዲደርሱ ያስችላል።

ምቹ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እና የአቪዬሽን ብቃት ደግሞ ሌላኛው ሚናው ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ካርታ ላይ ያላት ስልታዊ አቀማመጥ (በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ መገናኛ መስመር ላይ መገኘቷ) አቡሴራን ለዓለም አቀፍ በረራዎች አጭርና ተመራጭ የመሸጋገሪያ መስመር ያደርገዋል።

የአቡሴራ ከፍታ ከአዲስ አበባ ቦሌ ያነሰ በመሆኑ፣ የዓለም አቀፍ በረራ አውሮፕላኖች ሙሉ ነዳጅና ጭነት ይዘው ረጅም ርቀት በቀጥታ እንዲበሩ ሰፊ የአቪዬሽን ምቹነትን ይሰጣል። የአውሮፕላኖች የመጫን አቅምን ጨመረ ማለት ነው።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንደስትሪ ውስጥ እንደ ዱባይ (DXB) እና ሲንጋፖር (Changi) ያሉ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ማዕከላት ተርታ ያሰልፋታል።

በአጠቃላይ ሲታይ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ስልታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከማጠናከሩ ባሻገር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ፍጥነት የሚያሳልጥ ታላቅ ብሔራዊ ትሩፋት ነው።

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.