Logo
FBC
ሰላም! እንደምን አደራችሁ?

አካባቢ ጥበቃ…

የአካባቢ ጥበቃ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በታዳሽ ሃይል ማስፋፊያ እና በኤሌክትሪክ ተንቀሳቃሽነት የአየር ንብረትን ለመጠበቅ በስፋት እየሰራች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ብክለት ምንም ድርሻ ሳይኖራቸው ተጎጂነቱን ግን ካደጉት ሀገራት እኩል ሲጋሩ ኖረዋል፡፡

ለዚያም ነው የጋራ ወደፊትን ለመጠበቅ ትብብር አስፈላጊ ነው በሚል ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከራሷም አልፋ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭን እንዲጋሩ እያደረገች ያለችው፡፡

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት ይነገራል፡፡

በወቅቱ በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም የደን ሽፋናችን ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መራቆት እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጀመረ፡፡

ከዚያን ዓመት ጀምሮ እንደ ሀገራዊ ንቅናቄ በመያዝ በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የመትከልና የመንከባከብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 4 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

በ2012 ዓ.ም 5 ነጥብ 9 ቢሊየን፣ በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 ቢሊየን፣ በ2014 ዓ፣ም 7 ነጥብ 2 ቢሊየን፣ በ2015 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 ቢሊየን፣ በ2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 8 ቢሊየን ችግኝ የተተከለ ሲሆን÷ በ2018 ዓ.ም ዘንድሮ ደግሞ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአንደኛው እና በ2ኛው ምዕራፍ የተተከሉ ችግኞችን 50 ቢሊየን ለማድረስ ግብ ተጥሏል፤ ይህ ተግባርም ሀገራችን በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሐ ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

የፕሮግራሙ ውጤታማነት እና ስኬት የተገኘው ሥራውን ሀገር አቀፍ በማድረግ፣ በርካታ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ በማሳተፍ ነው፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ካለው ሀገራዊ የልማት ፋይዳ ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት፣ አድናቆት እና ምስጋና ያገኘ ሲሆን÷ ሌሎች ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ለሚያደርጉት ጥረት ፕሮግራሙን በሞዴልነት መከተል ጀምረዋል፡፡

ለዚህም ነው ለእኛ የአካባቢ ጥበቃ የህልውና ጉዳይ ነው የምንለው፡፡

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.