Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና)አሜሪካና ኢራን በ24 ሰአታት ውስጥ የሰላም ስምምነት እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች፡፡ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻህባዝ ሸሪፍ በአሜሪካና በኢራን መካከል ስምምነቱ በ24 ሰአታት ውስጥ እንደሚከናወን ገለፁ፡፡ ሚኒስትሩ በኤክስ ገፃቸው ላይ ‹‹ለወራት የዘለቀውን የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ለማስቆም በሚችለው የሰላም ረቂቅ አሜሪካና ኢራን ስምምነት ላይ ደርሰዋል›› ያሉ ሲሆን ፓኪስታን አሁን የኤሌክትሮኒክስ መፈራረሚያ ሰነድ እያዘጋጀች እንደምትገኝ አስታውቀዋል፡፡

በኤሌክትሮኒክስ የሚደረገው ይህ ስምምነት በሚቀጥሉት 24 ሰአታት ውስጥ እንደሚፈረም ገልፀውም በመጪው ሳምንት ደግሞ በከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የቴክኒክ ውይይቱ እንደሚጀመር አስረድተዋል፡፡ ጨምረውም ሁለቱም አገራት በቀጠናውና በአለም ሰላም እንዲመጣ በድርድሩ ወቅት ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ አሜሪካና ኢራን በነገው እለት በከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በስምምነት ሰነዱ ላይ ይፈራረማሉ፡፡

በዚህ የፊርማ ስነስርአት ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንቱ ጄዲ ቫንስ እንደሚገኙና ከኢራን በኩል ደግሞ የፓርላማ አፈጉባኤው መሀመድ ባክር ጋሊባፍ እንደሚወከሉ የጠቀሰው ዘገባው የፊርማው ቦታ ምናልባትም ጄኔቭ እንደሚሆን አስረድቷል፡፡ የስምምነት ሰነዱ ምን እንዳካተተ የተባለ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አግካራቺ በአገራቸው ቴሌቪዥን ባሰሙት ንግግር ‹‹በስምምነቱ ስትራቴጂያዊ ስኬት አግኝተናል፡፡ በጦርነቱ ኢራን አሸንፋለች›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

9 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.