Logo
EBC
አዲስ አበባ - የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የስፖርት ውድድሮች ተመራጭ ከተማ
****************

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባከናወናቸው ግዙፍ የስፓርት መሠረተ ልማት ግንባታዎች ምክንያት መዲናዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በስፋት የሚስተናገዱባት ቀዳሚ ተመራጭ የስፖርት ማዕከል መሆን ችላለች።

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተገነቡት ከ1 ሺህ 580 በላይ የሕዝብ እና የወጣቶች ስፖርት ማዕከላት ማኅበረሰባዊ ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ትልቅ መሠረት ተጥሏል።

በቅርቡ በታላቅ ድምቀት የተጠናቀቀው እና በመስቀል አደባባይ የተካሄደው 19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ከተማዋ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የብስክሌት፣ የአትሌቲክስ፣ የጎዳና ላይ ሩጫ እና ሌሎች የስፖርት ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ መዲናዋ ምቹ እና ተመሪጭ ከተማ መሆንዋን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

አዲስ አበባ አሁን ላይ የስፖርት ልሂቃን መገናኛ፣ የትላልቅ ውድድሮች እና የደጋፊዎች ድምቀት የምታስተናግድ ደኅንነቷ የተጠበቀ እና ውብ መዲና ሆናለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑት የተቀናጁ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዕከላት መስፋፋት የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

ይህ የስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ከስፖርታዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ለሆቴል ኢንዱስትሪው፣ ለትራንስፖርት ዘርፉ እና ለአካባቢው አነስተኛ እና ጥቃቅን የንግድ አንቀሳቃሾች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መነቃቃትን ፈጥሯል።

ይህም የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የያዘውን ግብ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፈው እንደሚገኝ ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#ethiopia #ebc #addisababa #sports

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.