Logo
EBC
በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ሳቢያ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ሊቀንስ ይችላል
**********************

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ጂኦፖለቲካዊ ቀውስ የዓለምን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየናጠው እንደሚገኝ ተጠቁሟል። የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በአወጡት የኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት፣ በግጭቱ ሳቢያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት እ.አ.አ. በ2026 የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ሊቀንስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የዓለም ባንክ ቀደም ሲል አስቀምጦት የነበረውን የ2026 የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ግምት ወደ 2.5 በመቶ ዝቅ አድርጎታል።

ይሁን እንጂ የግጭቱ መባባስ የኃይል አቅርቦት መስተጓጎልን ካስከተለና የፋይናንስ ገበያው ውጥረት ውስጥ ከገባ፣ ዕድገቱ እስከ 1.3 በመቶ ድረስ ሊወርድ እንደሚችል ባንኩ ጠቁሟል። ይህም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ ዓለም ላይ የሚከሰት ዝቅተኛው የዕድገት ምጣኔ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት የዋጋ ንረትን እያባባሰ መሆኑን አመልክቷል።

በችግሩ ምክንያት የሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ መጨመር የሸቀጦችን ዋጋ በ22 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በተለይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ በሚያስገቡ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።

በሌላ በኩል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ ላይ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን መልሶ ሊያነቃቃውና ለምርታማነት መጨመር ትልቅ ድጋፍ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።

የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ መጪውን የኢኮኖሚ ፈተና ለመቋቋም ሀገራት በኢነርጂ እና በምግብ ዋስትና ዙሪያ በጋራ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በላሉ ኢታላ
#ethiopianbroadcastingcorporation #world #economy

15 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.