Logo
YenetaTube
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ነገር ሁሉ ትከልለን፤ ምልጃዋ እና ረድኤቷም አይለየን🙏

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢቱ ኢሳ 7፡14 "ድንግል ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች" ብሎ የተናገረላት ያቺ ድንግል በዚህች ዕለት ተወለደች፡፡ ይህች ቀን ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝ 44÷9 "የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች" ብሎ የተናገረላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘችባት ናት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራዕይ 12÷1 "ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አስራ ሁለት የክዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት" ብሎ የመሰከረላት የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ የእርስዋም ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን ሲገለጽ የነበረ መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ያስረዳናል፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን (የግንቦት ልደታ) የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ‹‹የመመኪያችን ዘውድ፣ የንጽሕናችንም መሰረት›› ያላት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተወለደችበት ነው፡፡ ጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን በመኃልይ 4÷8 "ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፡ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፡፡" ብሎ እንደተናገረ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሰረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በ15 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት "ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ/ ማርያም ግን ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡ በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል።

ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሰሎሞን እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን ስለእመቤታችን የተናገረውን ቃል መፈጸሙን ሲያመሰጠር "የአናብስት ልጅ አልኩሽ፡፡ ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ ተራራ ነዪ፤ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ፤ ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው፡፡" ይላል፡፡ እመቤታችንም በሊባኖስ ተራራ እንድትወለድ ምክንያት የሆነው በማሕፀን ሳለች የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሳቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ስለነበር ሐናና ኢያቄም ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሄዱ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ስለነገራቸው እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ስለታላቅ መንፈሳዊ ተልዕኮ ሲባል ከሚያውቁት ቦታ መራቅን፣ ከለመዱት ቀዬ መሰደድን ከእመቤታችን የተረዱት ገዳማውያንም ዓለምን ንቀው ስሟን ስንቅ አድርገው ይመንናሉ። ገዳማቸውን ስንደግፍ ፣ በዓታቸውን ስናጸና የበረከታቸው ተሳታፊ እንሆናለን።

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957

6 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.