Logo
FastMereja
በቡኢ ከተማ አሽከርካሪውን ገድለው ባጃጅ ዘርፈው የነበሩት በወልቂጤ ከተማ በቁጥጥር ስር ዋሉ

​#fastmereja I ​በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ ላይ ባለፈው የካቲት ወር የባጃጅ አሽከርካሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ በመ ግደል ተሽከርካሪውን ዘርፈው ተሰውረው የነበሩ ተጠርጣሪዎች፤ የወልቂጤ ከተማ ላይ ያለ ሰነድ ሊሸጡ ሲሉ የቀቤና ልዩ ወረዳ ፖሊስ እጅ ከፎቅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

​የቀቤና ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ወለላ ኤልያስ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ አሽከርካሪውን ሙሉቀን አምበሴን ለሰርግ አገልግሎት እንፈልጋለን በማለት ካታለሉ በኋላ፣ አዳዘር ቀበሌ ልዩ ስሙ ጉቹሞተቤ ወደሚባለው ጫካ በመውሰድ በጭካኔ ገ ድለውታል። በመቀጠልም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-01110 የሆነውን ባጃጅ ዘርፈው ወደ ወልቂጤ ከተማ በመውሰድ በአንድ ጋራዥ ውስጥ ደብቀውት እንደነበር ተገልጿል።

​ተጠርጣሪዎቹ ያለ ሊብሬና ያለ ምንም ህጋዊ ሰነድ ባጃጁን በ150 ሺህ ብር በድርድር ለመሸጥ ሲያስማሙ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ መነሻነት ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከነባጃጁ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በልዩ ወረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ምርመራ ሲካሄድባቸው የቆየ ሲሆን፤ በከባድ የነፍስ ማጥፋትና በዘረፋ ወንጀል ሲፈለጉ ለነበሩት ለምስራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ተላልፈው ተሰጥተዋል።

​የቡኢ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አልማዝ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ከተገደለ ከሁለት ቀን በኋላ የካቲት 3 ቀን በጥቃቅን አራዊት ተበልቶ የተገኘው የሟች አስክሬን በሰው መገደሉን የሚያሳዩ ፍንጮች በመገኘታቸው ልዩ የመርማሪ ቡድን ተዋቅሮ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። ወንጀል ሰርቶ መሰወር እንደማይቻል ያሳየ ስራ ለሰሩት የቀቤና ልዩ ወረዳ ፖሊስና ህብረተሰብ ምስጋና ያቀረቡት ኢንስፔክተሯ፤ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን ወደ ፈጸሙበት ቡኢ ከተማ ተወስደው ምርመራቸው ተጠናቆ ህግ ፊት እንደሚቀርቡ አረጋግጠዋል።

6 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.