Logo
Getu Temesgen
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፍራንስ 24 ምርጫውን አስመልክቶ በሰራው ዘገባ ላይ የአዲስ አበባን ልማት “አስከፊ” ብሎ በመፈረጅ ያሰራጨው ዘገባ የያዛቸው መረጃዎች “ከእውነት የራቁ ናቸው” አለ
#ethiopia | በፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ፍራንስ 24 ባለፈው ሰኞ የተካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ በሰራው ዘገባ “ምርጫውን የይስሙላ” እንዲሁም የአዲስ አበባን ልማት “አስከፊ” ሲል መግለጹ፣ ኢትዮጵያ ያለችበንት ሁኔታ እና እውነታ ያላገናዘበ ነው ሲል የተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል።

ኤምባሲው ፍራንስ 24 የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሳቢን ፕላኔል ከተባሉ “እንግዳ” ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ፤ የቀረቡትን ሀሳቦች፣ አሳሳችና ወገንተኝነት የተሞላባቸው ትችቶች ናቸው በማለት በጽኑ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡ ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ የጣቢያው ዘገባ የሀገሪቱን ነባራዊ እውነታም ሆነ የመንግሥትን ሰፊ ጥረቶች የማያንጸባርቅ አሳሳች ትርክት ነው ሲል ፈርጆታል።

አክሎም ባለፉት ዓመታት ተመዝግበዋል ያላቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስኬቶችን ወደ ጎን በመተው አስተዳደሩን በ“እርስ በርስ ጦርነት” ብቻ ከፋፍሎ ለመግለጽ የተደረገው ሙከራ ማጋነንና ከተጨባጭ እውነታ የራቀ መሆኑን ጠቅሷል። ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ቀጣናዊ ሁኔታዎች ውስጥም ሆና በዋና ዋና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተመሰከረለትን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና የመሠረተ ልማት ማዘመን ሥራዎችን “አስከፊ” ሲል የገለጸበትን አግባብ፣ ኤምባሲው ውድቅ እንደሚያደርገው በመግለጽ ይህ የልማት ፕሮጀክት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እየቀየረ ያለና በዋና ከተማዋም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ አድናቆት የተቸረው ስኬት ነው በማለት አወድሷል።

ኤምባሲው አክሎም በምርጫው ላይ ስለአሳታፊነትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አስመልክቶ የሰራውና የተቸበት መንገድ በስህተት የተሞሉ ናቸው ሲል በጽኑ ነቅፏል። የፈረንሳዩ የዜና አውታር በሰራው ዘገባ “በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግማሽ ያህሉ የምርጫ ክልሎች አልመረጡም” ማለቱን በተመለከተ ደግሞ ይህ መረጃ ሙሉ በሙሉ ሐሰት መሆኑን ኤምባሲው በአሐዛዊ መረጃዎች አስደግፎ ተከላክሏል።

ለአብነትም “በአማራ ክልል ከ138 የምርጫ ክልል በስምንቱ ብቻ አለመካሄዱን በመጥቀስ፣ ይህም ከክልሉ አጠቃላይ ቁጥር 6 በመቶ ብቻ መሆኑን” አመልክቷል።

እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና አጠቃላይ ሂደቱ ዲሞክራሲን የተከተለ መሆኑን በመግለጽ መገናኛ ብዙኃኑ የሰራቸው እና ያሰራጫቸው መረጃዎች እውነታን ያላገናዘቡ ናቸው ሲል አጣጥሏል፡፡

ምርጫው በተለይም በዴሞክራሲ ምህዳር መስፋትና መገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ ዙሪያ የይስሙላ እንደነበር በዘገባው መጠቀሱን ያወሳው መግለጫው፤ የተመራጮችን፣ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ታዛቢዎችን፣ የሚዲያ ብዛት እና የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ቁጥር እንዲሁም በአጠቃላይ ምርጫው ላይ ያሉ ቁጥሮችን በመጥቀስ ውድቅ አድርጎታል።

ኤምባሲው አክሎም ሚዲያው የውጭ ወገኖችን ማለትም የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድን ታዛቢዎችን ሚና ለማሳነስ “ትላልቅ ግድፈቶችን ሪፖርት አያደርጉም” ማለቱ የተቋማቱን ስራ ማሳነስ ነው ብሎታል ። የሁለቱንም ተቋማት ልዑካን የሚመሩትን ኃላፊዎች ማንነት በመግለጽ አንጋፋ ተቋማትና መሪዎችን ማጣጣል የአስተሳሰብ አድሏዊነት ማሳያ ነው በማለት ኮንኖታል።

በመጨረሻም የዚህ ምርጫ ውጤት የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በራሱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንጂ ከውጭ በሚሰጡ መግለጫዎችና አስተያየቶች አይደለም ሲል አስታውቋል።
#አዲስ_ማለዳ

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.