Logo
FastMereja
“በአማራ ክልል 8 ምርጫ ክልሎች ምርጫ አልተካሄደም” የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ የቅኝት ሪፖርት ይፋ አደረገ
#fastmereja I የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያደረገውን አጠቃላይ የንቅናቄና የቅኝት ስራ በተመለከተ ሰፋ ያለ መግለጫ የያዘ ይፋዊ የግምገማ ሪፖርት አውጥቷል። ፌዴሬሽኑ በምርጫው ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን፣ የተመዘገቡ ስኬቶችን፣ ያጋጠሙ የጸጥታና የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ለቀጣይ ምርጫዎች የሚረዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አስታውቋል።

ፌዴሬሽኑ በምርጫው ወቅት ከ25,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን የሸፈነ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 14,160 ታዛቢዎችን (11,382 ቋሚ እና 2,241 ተንቀሳቃሽ) በማሰማራት ሰፊ የቅኝት ስራ ማከናወኑን አስታውቋል። በዚህም የምርጫው ሂደት በሴቶች ተሳትፎ፣ በጸጥታ ሁኔታ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በድህረ-ምርጫ ሒደት ምን እንደሚመስል ዝርዝር ግምገማ አቅርቧል።

በፌዴሬሽኑ ሪፖርት መሠረት በምርጫው ዝግጅትና አፈጻጸም ወቅት በርካታ አዎንታዊ ተሞክሮዎችና ጥንካሬዎች ተመዝግበዋል። የምርጫው ሂደት በአብዛኛዎቹ ክልሎች በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁ፣ የሕዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑ እና በድምፅ መስጫ ቀንም ሆነ በድህረ-ምርጫ የቆጠራ ሂደት ላይ የፓርቲ ወኪሎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ታዛቢዎች በንቃት መሳተፋቸው በበጎ ጎኑ ተጠቅሷል። በተለይም የሴቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ የተገለጸ ሲሆን፣ አጠቃላይ ከተመዘገቡት መራጮች ውስጥ 49.3 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንና የሴት ዕጩዎች ቁጥርም ካለፉት ምርጫዎች አንጻር መሻሻል ማሳየቱ በጠንካራ ጎንነቱ ተቀምጧል። የጸጥታ አካላትም የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥና ግጭቶች እንዳይባባሱ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሚና መጫወታቸውን ፌዴሬሽኑ በምስጋና ገልጿል።

በሌላ በኩል በምርጫው ሂደት ውስጥ የታዩ መዋቅራዊና የአፈጻጸም ድክመቶች በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር ተመልክተዋል። በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ የዲጂታል ምዝገባና የመረጃ ማስተላለፍ ስራዎች መጀመራቸው መልካም ቢሆንም፣ ቴክኖሎጂው ከመደበኛው አሰራር ጋር ሙሉ በሙሉ አለመቀናጀቱና ቅድመ-ሙከራ አለመደረጉ በተለይ በአዲስ አበባ ረጅም ሰልፎችንና የመራጮች መጉላላትን ፈጥሯል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የተኩስ ድምፅ መሰማቱና የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙ፣ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በአማራ ክልል በ8 የምርጫ ክልሎች ምርጫ አለመካሄዱ፣ እና በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በድምሩ በ7 ጣቢያዎች ምርጫ መቋረጡ ተገልጿል።

በአማራ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ አዲስ አበባና አፋር ክልሎች ደግሞ አንዳንድ ጣቢያዎች በሰዓቱ አለመከፈታቸውና በጋምቤላ ክልል አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መራጮችን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለማስመዝገብ መሞከራቸው በደካማ ጎንነት ተጠቅሰዋል።

ፌዴሬሽኑ ያጋጠሙትን ችግሮች መሠረት በማድረግ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት የቀጣይ የውሳኔ ሃሳቦችንና ምክረ-ሀሳቦችን አቅርቧል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ሰፊ ቅድመ-ሙከራ እንዲያደርግ፣ የቁሳቁስ አቅርቦትን አስቀድሞ እንዲያጠናክር፣ ለአስፈጻሚዎች በቂ ስልጠና እንዲሰጥና ለጋዜጠኞችና ታዛቢዎች ግልጽ መመሪያ እንዲያዘጋጅ ጠይቋል። ለመንግሥትና ለጸጥታ አካላት ደግሞ በአማራ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ የጸጥታ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱና ለሴቶችና አካል ጉዳተኞች ምቹ የምርጫ አካባቢ እንዲፈጠር አሳስቧል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በበኩላቸው በውስጥ ደንባቸው መሠረት ቢያንስ 30 በመቶ የሴት ዕጩዎችን እንዲያቀርቡ፣ የመራጮችን ነፃነት እንዲያከብሩና ሕገ-ወጥ ምዝገባዎችን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርቧል።

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.