Logo
YenetaTube
ለአትሌቶች አበረታች ቅመም በሚሰጡ ግለሰቦች ላይ የ7 ዓመት እስራት እና የ500 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣል ተገለጸ

የተከለከሉት ቅመሞች በሴት አትሌቶች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላሉ ተብሏል

ለአትሌቶች የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን የሚሰጡ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታውቋል።

በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የታገዙ የረቀቁ የዶፒንግ ማጭበርበር ስልቶችን ለመግታት ተቋማዊ የቁጥጥር አቅሙን እያሳደገ የሚገኘው ተቋሙ፤ ማንኛውም ግለሰብ ለአትሌቶች አበረታች ቅመሞችን ሲሰጥ ከተገኘ 7 ዓመት ፅኑ እስራት እና የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቀው አብራርቷል።

አበረታች ቅመሞችን ለራሱ የተጠቀመ ስፖርተኛ ደግሞ ከ2 ዓመት በሚበልጥ እስራት እስከ መቀጣት እና ከስራ እስከመታገድ የሚደርስ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በአዳማ ከተማ በተካሄደው የስፖርት ጋዜጠኞች መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የቁጥጥር ብቃቱን ከጊዜው ጋር ለማራመድ እየሰራ ይገኛል።

ይህ የመከላከል አቅም ማደግ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የስፖርት ተወዳዳሪነት እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ተብሏል።
በአሁኑ ወቅትም ሕገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አትሌቶች እና ሌሎች አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

እነዚህ የተከለከሉ ቅመሞች በተለይ በሴት አትሌቶች ላይ የወንዳዊ ገፀ ባህሪ፣ የጡት እድገት ማቆም፣ የጉበት እና የማህፀን በሽታዎች እንደሚያስከትሉ ተገልጾአል።

ደረጄ መንግሰቱ

10 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.