Logo
Getu Temesgen
የም/ቤቱ 23ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል
#ethiopia | ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም፤ የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄዳል።

ምክር ቤቱ በነገው ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን ለማፅደቅ የወጡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በሴራሊዮን ሪፐብሊክ፣ በአንጎላ ሪፐብሊክ፣ በባንግላዲሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ እንዲሁም በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥታት መካከል የተፈረሙትን የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆች አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ያፀድቃል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም የኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ያፀድቃል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ፣ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ፣ የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ፣ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል ያለው መናኸሪያ ኤፍ ኤም ነው።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

14 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.