Logo
EBC
የ54 ሚሊዮን ዜጎች ድምጽ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲሱ አቅጣጫ
*******************
(የዕለቱ መልዕክት)

ለዘመናት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥርጣሬ ዉስጥ መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። ዛሬ ግን ያ የድሮው መንገድ አክትሞለታል። የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ አዲስ ተስፋ ይዞልን መጥቷል፤ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት፣ በተለይ ደግሞ ከእነዚህም ዉስጥ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ በ“ምርጫዬ” ዲጂታል መድረክ ስማቸውን ያሰፈሩበት ይህ ሂደት፣ ሀገራችን ከጎዳና ጫጫታ ወደ ውይይት መድረክ፣ ከስሜት ወደ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር መሸጋገሯን በግልጽ ያሳያል።

በዚህ ምርጫ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከ10 ሺህ በላይ እጩዎችና 80 የግል ተወዳዳሪዎች በአንድ የህግ ጥላ ስር ቆመው፣ በምርጫ ስነ-ምግባር ሕግ ተሳስረው ለመወዳደር መዘጋጀታቸው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መለያ ነው።

ይህ ምርጫ የአንድ ቀን የድምፅ መስጠት ተግባር ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የዴሞክራሲ ትርጉም ከፖለቲካ ልሂቃን ጠባብ አዳራሾች ወጥቶ ወደ ህዝብ ልብና ህሊና እየገባ መሆኑን የሚያበስር ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።

ውድድሩ ከብሽሽቅ ወደ ፖሊሲ ክርክር አድጓል። በርካታ የሕዝብ ውይይት መድረኮች በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው መቅረባቸው አካታችነትን በተግባር ያሳየ፣ የተፎካካሪና የገዢ ፓርቲዎችን እኩልነት በገሃድ ያረጋገጠ፤ የተቋማዊ ብስለት የታየበት እርምጃ ነው።

ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎችን በኩራት ጋብዞ፣ የአፍሪካ ህብረትንና የኢጋድን ታዛቢዎችን በማሳተፍ አፍሪካ የራሷን ጉዳዮች በራስ አቅም የመመልከት አቅሟን ያሳየችበት እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ምርጫን ለማካሄድ መነሳት ራሱ ትልቅ ታሪካዊ ድል ነው። እንደ ኡሁሩ ኬንያታ ያሉ የአህጉሪቱ አንጋፋ መሪዎች የታዛቢ ቡድኖችን ይዘው መግባታቸው የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጥረት በአፍሪካ መድረክ ከፍ አድርጎታል።

መልዕክቱ ግልጽ ነው፤ ፖለቲካ በሀይል ሳይሆን በህዝብ ድምፅ፣ በስሜት ሳይሆን በውይይት፣ በመገለል ሳይሆን በብሔራዊ ተሳትፎ ሊመራ እንደሚችል በተግባር እያሳየን ነው።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ትልቁ ድል የትኛው ፓርቲ አሸነፈ የሚለው ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብና ተቋማት በዴሞክራሲያዊ ብስለት ማሸነፋቸው ነው።

ይህ የዲጂታል ዘመን ትውልድ የሀገሩን እጣ ፈንታ በራሱ እጅ እየጻፈ ነው። የነገዋን የበለፀገችና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በሰላም፣ በህግና በውይይት መስመር ላይ እናጽና፤ ምክንያቱም የነጻነትና የፍትህ መሠረቱ የህዝብ ድምፅ ብቻ ነውና።

ኢትዮጵያ ትመርጣለች!
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

Ethiopian Broadcasting Corporation #ethiopiavotes #democracy #ethiopia

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.