Logo
FastMereja
የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለአለም ለማስተዋወቅ አዲስ አህጉር አቀፍ ዘመቻ ይፋ ሆነ!
#fastmereja I የአፍሪካን አዎንታዊ ገጽታ፣ የፈጠራ ስራዎችን፣ ንግዶችንና አህጉራዊ እድገትን ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ «#notwaiting» (አፍሪካ አትጠብቅም) የተሰኘ አዲስ ህዝባዊ ንቅናቄ ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም በሚከበረው የአፍሪካ ቀን በይፋ መጀመሩ ተገለፀ።

በኦፖርቹኒቲ አፍሪካ (Opportunity Africa) አስተባባሪነት የተጀመረው ይህ ዘመቻ፤ አፍሪካውያን ስለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት መቀየር ከቻሉ፣ ዓለምም ስለ አፍሪካ ያላትን የተዛባ አመለካከት ይቀይራል በሚል ጽኑ እምነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል።

የአፍሪካ ኖ ፊልተር(Africa No Filter) ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሞኪ ማኩራ እንደገለጹት፣ ዓለም ስለ አፍሪካ ያለው አሉታዊ እና የተዛባ አመለካከት በአህጉሪቱ ላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ቅጣት ወይም የ«ስጋት ዋጋ» (Risk Premium) እያስከተለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለዉም ይህ አመለካከት ወደ አህጉሪቱ ሊፈስ የሚችለውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት የሚያሰናክል ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የአገር ውስጥ ንግዶችና ተራው ዜጋ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የብድር ወለድ ገንዘብ ለመበደር እንዲገደዱ አድርጓል። ይህ ንቅናቄ ይህንን የተዛባ ምልከታ በመቀየር የኢኮኖሚ ጫናውን ለማቃለል ያለመ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ሞኪ ማኩራ ከስድስት ወይም ሰባት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ያዩትን ተጨባጭ ሁኔታ ያጋሩ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የታየው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት «አስደናቂ» መሆኑን ገልጸዋል።

የአሁኗን በማደግ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ በ1984-1985 ከነበረውና የአጠቃላይ አህጉሪቱን ገጽታ ለትውልድ አበላሽቶ ከቆየው አስከፊ የረሃብ ምስል ጋር በማነፃፀር፤ ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጥንካሬና ጽናት ከአመድ ላይ ተነስታ ለዳግም እድገት የበቃች ምርጥ የአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን ገልጸዋል።

ይህ ንቅናቄ በአፍሪካ የሚገኙ ስራ ፈጣሪዎች፣ የባህልና የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም የአገር በቀል ተቋማት መሪዎች ከማንም እርዳታ ሳይጠብቁ በየቀኑ ሀገራቸውን ወደፊት እየገፉ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር የሆኑት ፌዝ አዲያምቦ እንደገለጹት፦ ይህ ዘመቻ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ እንዲታወቅለት፣ እንዲረጋገጥለት ወይም በሌሎች እንዲበየን የማይጠብቅ አዲስ ትውልድ የተሞላበትን ጉልበት ያሳያል ያሉ ሲሆን አፍሪካውያን የሚፈልጉትን የወደፊት እጣ ፈንታ ራሳቸው እየገነቡ ነው፤ ይህ ዘመቻ ደግሞ ይህንን እውነታ ለራሳችንም ሆነ ለዓለም ይፋ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

አፍሪካ ሁሌም ራሷን በጉድለትና በችግር ትረካዎች ውስጥ እያየች በልበ ሙሉነት መገንባት አትችልም ሲሉ ገልጸው፣ የአፍሪካ ገጽታ መቅረጽ ያለበት በራሷ ህዝቦች እንጂ ከውጭ በሚጫንባት የተዛባ አመለካከት መሆን የለበትም ብለዋል።

ይህ ዘመቻ በየወሩ በ25ኛው ቀን (በአፍሪካ ቀን መታሰቢያነት) በየጊዜው የሚደገም ሲሆን፣ አፍሪካውያንና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የኢንተርኔት ገጾችን በአዎንታዊ የዕድገት፣ የፈጠራ እና የስራ ፈጠራ ታሪኮች እንዲያጥለቀልቁት ተጋብዘዋል።

10 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.