Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከባህር ማዶ መጥቶ እንደ ግብጹ "የአባይ ውሃ ዘመዳችን" መሀመድ ሳላህ የጎል መረብን ያንቀጠቀጠ የለም፤ 193 የማይታመኑ ጎሎች! ታሪኩ የሚጀምረው ነሐሴ 12 ቀን 2017 ነው። ሊቨርፑል ዋትፎርድን ሲገጥም፣ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ አዲስ ፈራሚውን «ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንኳን በደህና መጣህ!» በሚል አጭርና ግልጽ መልዕክት ወደ ሜዳ ሰደዱት። ያኔ የተጠነሰሰው አስፈሪው የሳላህ፣ ማኔ እና ፊርሚኖ የአጥቂ መስመር ጥምረት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላን ጭምር «ያናውጡኛል፣ አደገኞች ናቸው» እስኪል ድረስ ዓለምን ጉድ አሰኝቷል።

ሳላህ እና ማኔ የቅርብ ጓደኛሞች ባይሆኑም፣ በመካከላቸው የነበረው ጤናማ ውድድር እና ፊርሚኖ በሁለቱ መሀል የሚነሳውን እሳት በማጥፋት የተጫወተው ሚና፣ የሊቨርፑልን የድል ጉዞ የጀርባ አጥንት ሆኗል። የቡድኑ አጋሮቹ «ለእግር ኳስ የተፈጠረ» ብለው የሚመሰክሩለት ሳላህ፣ በምሳሌነት የሚመራ [ይላል] እና ለዝርዝር ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ጽኑ ተዋጊ ነው። ዋትፎርድን 5 ለ 0 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ፣ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ግብ ጠባቂውን ቤን ፎስተርን «ፍጹም ቅጣት ምት ቢሆን ኖሮ ወደየትኛው አቅጣጫ ትዘል ነበር?» ብሎ መጠየቁ ለስራው ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

በአንፊልድ ቆይታው አንዳንዴ ተስፋ መቁረጥ እና ቁጣ ታይቶበት ያውቃል። ባለፈው ታህሳስ ከዋና አሰልጣኙ አርኔ ስሎት ጋር የነበረው አለመግባባት አሁን ላለው ስንብት መነሻ ሆኗል። ይህ የውድድር ዘመን ለሊቨርፑል ስብስብ እጅግ ከባድ የነበረ ሲሆን፣ የቡድን አጋሩ ዲዮጎ ጆታ ህይወት ማለፍ ሳላህን ክፉኛ ጎድቶታል። «ከእረፍት በኋላ ወደ ሊቨርፑል መመለስ እንደዚህ ያስፈራኛል ብዬ አስቤ አውቅም» ሲል ሀዘኑን ገልጾ፣ በአንፊልድ ፊት እምባውን በማፍሰስ ሰብዓዊነቱን አሳይቷል።

በሜዳ ላይ ግን ሳላህ ከተፈጥሮ በላይ ነበር። በአንፊልድ የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ 58 የጎል ተሳትፎዎችን (በየ 71 ደቂቃው አንድ ጎል ላይ ተሳትፎ) በማድረግ ሜሲ እና ሮናልዶ ካሉበት ደረጃ ደርሷል። ማድሪድ ላይ ቶተንሃምን አሸንፈው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሲያነሱ፣ በጉዲሰን ፓርክ ኤቨርተን ላይ የፑስካስ አዋርድ ያሸነፈባትን ጎል ሲያገባ፣ እና በኦልድ ትራፎርድ ማንችስተር ዩናይትድ ላይ ያሳየው ጀብዱ... ትዝታዎቹ ማለቂያ የላቸውም። የሲቲው አይሜሪክ ላፖርት ጭምር «ሳላህ በእኛ ላይ ሁልጊዜ እሳት ይተፋ ነበር፤ ለመከላከል ከገጠሙኝ ከባድ ተጫዋቾች አንዱ ነው» በማለት ይመሰክራል።

ሸሚዙን አውልቆ ደስታውን ሲገልጽም ሆነ በሱጁድ ፈጣሪውን ሲያመሰግን፣ የሳላህ ምስሎች መቼም አይረሱም። የቀድሞው አምበል ስቲቨን ጀራርድ «ቁጥሮቹ፣ ዋንጫዎቹ እና የገነባው ባህል የራሳቸው ታሪክ ይናገራሉ። መሀመድ ሳላህ በሁላችንም ዘንድ የተወደደ የክለቡ እውነተኛ ጀግና ነው» ሲል አወድሶታል። ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድም ለክለቡ ያላቸውን ዋጋ ሲገልጽ ሳላህን እና ጀራርድን በእኩልነት አንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል።

የ2024-25 የውድድር ዘመን ሊቨርፑል 20ኛውን የሊግ ዋንጫ ሲያነሳ፣ ሳላህ ከፍተኛ ጎል እና አሲስት በማድረግ በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ አሳርፏል። አሁን ግን ሁሉም ነገር ፍጻሜ አለው። ከግብጽ የናይል ዴልታ የተነሳው የዚህ ድንቅ ተዋጊ ጉዞ፣ በሜርሲሳይድ አንፊልድ ላይ የማይረሳ ታሪክ ጽፎ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የርገን ክሎፕ እንዳሉት፣ «ሲመጣ ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ሳይሆን፣ ሲሄድ ምን እንደሚያስቡ ማወቁ ነው ትልቁ ነገር»። መሀመድ ሳላህ... ለአንፊልድ ትክክለኛው ተዋጊ፣ በትክክለኛው ጊዜ የመጣው ጀግና!

11 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.