Logo
YenetaTube
ከሚሰሩበት ድርጅት ውስጥ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ካሜራዎችን የሰረቁ ተከሳሾች በ7 ዓመት ከ6 ወር እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡

ተከሳሾች ዘሪሁን አበበ እና ሄኖክ አማረ ወንጀሉን የፈፀሙት ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ/ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው አራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ህንፃ ላይ ከሚገኝ አንድ የፊልም ስራዎች ኮሌጅ ነው፡፡

ተከሳሾች በኮሌጁ ውስጥ በጥበቃ ሠራተኝነትና በህንፃ እድሳት ስራ ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆኑ የቢሮውን ቁልፍ በማስቀረፅ ሰው ያለመኖሩን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጠቅላላ ግምታቸው ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 2 ቪድዮ ካሜራዎች፣ 2 የካሜራ ባትሪ፣ 1 የካሜራ ቻርጀር እንዲሁም 2 ኒክ ማይክ በመስረቅ ወንጀላቸውን ለመደበቅና ከውጭ ሌባ ገብቶ የሰረቀ ለማስመሰል ጣሪያውን በመቅደድ ወንጀሉን ፈፅመዋል፡፡

የግል ተበዳይ አልኣዛር ጥላሁን በድርጅታቸው የቤት ሰብሮ ወንጀል ከተፈፀመባቸው በኋላ 4 ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ በማመልከታቸው ፖሊስ ጠንካራ ምርመራና እና ክትትል በማድረግ ተከሳሾቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ንብረቶቹን እንዲመለስ በማድረግ በዐ/ህግ ክስ እንዲመሰረትም አድርጓል፡፡

የምርመራ መዝገቡን ሲከታተል የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ/ም በዋለው ችሎት ዘሪሁን አበበ እና ሄኖክ አማረ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል፡፡

የትኛውም ተቋምም ሆነ ግለሰብ የሰራተኛ ቅጥር በሚፈፅምበት ወቅት ጥንቃቄ በማድረግ ተቀጣሪዎች ያሏቸውን መረጃዎች እና ዋስትና በተገቢው ሁኔታ በማረጋገጥ መሰል ወንጀሎች ለመፈፀም ዕድል እንዳይኖራቸው ማድረግ ይኖርበታል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

Addis Ababa police

23 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.