Logo
FBC
የዳታ አያያዝን ለማዘመን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሚና ከፍተኛ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዳታ አያያዝን ለማዘመን የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ሚና ከፍተኛ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

‎''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት'' በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ የዳታ አያያዝን ለማዘመንና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን ለማሳለጥ ቴክኖሎጂ በተለይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሚናው ከፍተኛ ነው።

በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂዎች እርስ በርስ እየተቀናጁ በመምጣታቸው ነጣጥሎ ማየት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ስራ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዞ ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ስታቲስቲክስን፣ ግብርናንና ጤናን ከቴክኖሎጂ ውጭ ማሰብ ወደማይቻልበት ደረጃ መደረሱን ጠቅሰው፤ እያንዳንዱ ተቋም ቴክኖሎጂን በብቃት መጠቀም ሲችል የመረጃ ጥራት፣ ስፋትና ተደራሽነት እንደሚያድግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጠንካራ ስራ ሲሰሩ ከቆዩ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አንዱ መሆኑን አንስተው፤ ተቋሙ አሁን የደረሰበት የዲጂታላይዜሽን ደረጃ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የመረጃ ሰብሳቢዎችን የመገኛ ቦታ በአይፓድ በመከታተል፣ መረጃው በተቀመጠለት ጊዜ በመሰብሰብ እና ማንኛውንም እንከን በራሱ በሲስተሙ በመታገዝ ማረም የሚያስችል የዳታ ማረጋገጫ ስርዓት በመዘርጋት መሰራቱ በእጅጉ አጋዥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዳታና ወርቅ እኩል ዋጋ እንዳላቸው በማመን በፖሊሲ፣ በሕግ እና በእውቀት የሚመራ ማንኛውም ሀገርና መንግሥት ብልፅግናን ማረጋገጡ የማይቀር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

እያንዳንዱ ህግ፣ ፖሊሲና የስራ መዘርዝር በዳታና በእውቀት ላይ ተንተርሶ እንዲሰራ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዮናስ ጌትነት

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.