Logo
FastMereja
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመቱን በታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ አከበረ
#fastmereja I የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ ያዘጋጀው የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ዛሬ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም በልዩ ድምቀት ተካሄደ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ተቋሙ በታሪኩ መጀመሪያ በ1938 ዓ.ም ስራ ሲጀምር በጥቂት አነስተኛ አውሮፕላኖች ብቻ በረራ ያደርግ እንደነበር አስታውሰው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባደረገው ያልተቋረጠ እድገት በአሁኑ ወቅት የዓለምን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያካተቱ የተለያዩ የቦይንግ፣ የኤርባስ እና የሌሎች አውሮፕላኖች ባለቤት መሆን መቻሉን አብራርተዋል። አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ145 በላይ መዳረሻዎች እንዳሉት የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ በተለይም በካርጎ፣ በአቪዬሽን አካዳሚ ማሰልጠኛ እና በሌሎችም የዘርፉ አገልግሎቶች አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ይህ መዋቅራዊ ጥንካሬውና ስትራቴጂካዊ ዕድገቱ አየር መንገዱን ተመራጭና ቀዳሚ እንዲሆን እንዳስቻለውም አመልክተዋል።

አየር መንገዱ የ80 ዓመት ታሪካዊ የስኬት ጉዞውን የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫን ጨምሮ በፓናል ውይይቶች፣ በአውደ-ርዕዮች እና በተለያዩ ማህበራዊ ዝግጅቶች በታላቅ ድምቀት እያከበረ እንደሚገኝ ተገልጿል። በሩጫ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህንን ጨምሮ የአየር መንገዱ የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

መነሻውን ከሣር ቤት በማድረግ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማጠናቀቂያውን ያደረገው በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ላይ አትሌቶች፣ የአየር መንገዱ ሰራተኞች፣ የስፖርት ቤተሰቡ እና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ሰራተኞች ተሳትፏል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.