Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) "ባለፈው አመት ብቻ ለአፍሪካ ህብረትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ ፅፌ ነበር፡፡" ሲሉ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንቱን ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደን አባረው የክልሉ ፕሬዝደንትነት ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የፕሬዝደንትነት ስልጣኑን መልሰው ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የፕሪቶሪያን ስምምነት በመጣስ የፌዴራል መንግስቱን ከሰዋል፡፡

በንግግራቸው ስምምነቱ መጣስ የጀመረው የትግራይ ሀይሎች ከባድ መሳሪያቸውን በሚያስረክቡበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በስምምነቱ መሰረት ተመሳሳይ ግዴታዎች እንዳልተፈፀሙ አስረድተዋል፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን ሲናገሩ ‹‹ስምምነቱ የተጣሰው እኛ ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከብ ስንጀምር ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን ተከትሎ የፌዴራል መንግስቱ ከትግራይ ክልል ውስጥ የፌዴራል ያልሆኑና የውጭ አገር ወታደሮችን የማስወጣት ግዴታ ነበረበት›› ብለዋል፡፡

ሲቀጥሉም የፌዴራል መንግስት የነዳጅ አቅርቦትን፣ የክልል በጀት ዝውውርን፣ በባንኮች ውስጥ ጥሬ ገንዘብን በመከልከል በክልሉ ውስጥ የኢኮኖሚ ጫናን እንዳጠናከረ ገልፀው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከትግራይ አመራሮች ለሚቀርብለት ማሳሰቢያ መልስ ሊሰጥ እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡ ንግግራቸውን በመቀጠልም ‹‹ባለፈው አመት ብቻ እኔ አፍሪካ ህብረትንና ተመድን ጨምሮ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ 10 ጊዜ ደብዳቤ በመፃፍ የፕሪቶሪያን ስምምነት ለማዳን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቄያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ ምንም አይነት ውጤት አልመጣም›› በማለት ገልፀዋል፡፡ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን አስተዳደር ለመመለስ የፈለጉት በክልሉ ውስጥ ህገ መንግስታዊ አስተዳደርንና አስቻይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ደብረፅዮን ጨምረውም ‹‹ለትግራይ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ የሚሆነው ምርጫ ማካሄድ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው አለመረጋጋትና መፈናቀል የተነሳ ታማኝነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም›› ብለዋል፡፡ ከ45 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የትግራይ መሬት በወረራ ስር መሆኑንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስረድተውም በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ትግራይን ሊበታትን እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.