Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ "ታይቶ የማይታወቅ" መስተጓጎል በመፈጠሩ፣ ሀገራት የነዳጅ ክምችታቸውን እና ስትራቴጂካዊ ተቀማጭ ሀብታቸውን 'በታሪካዊ ፍጥነት' እየተጠቀሙበት መሆኑን ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ጦርነቱ መፈንዳቱን ተከትሎ በመጋቢት ወር 129 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከዓለም አቀፍ ክምችት ላይ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በሚያዝያ ወር ደግሞ ተጨማሪ 117 ሚሊዮን በርሜል መቀነሱን ኤጀንሲው ገልጿል። በተለይም ኢራን (ቴህራን) ስትራቴጂካዊ የሆነውን የሆርሙዝ ባህረ ሰላጤን የባህረ ሰላጤው አገራት የነዳጅ እና ጋዝ ኤክስፖርት እንዳያልፍበት በተግባር መዝጋቷን ተከትሎ፣ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። ይህም ሀገራት አማራጭ የነዳጅ አቅርቦቶችን ለማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሯሯጡ አስገድዷቸዋል።

ኤጀንሲው በወርሃዊ ሪፖርቱ ላይ እንዳስጠነቀቀው፣ ከቀጣይ የአቅርቦት መስተጓጎል ጋር ተዳምሮ በፍጥነት እያሽቆለቆለ የመጣው የነዳጅ ክምችት፣ በቀጣይ ለሚፈጠር ከፍተኛ የዋጋ ንረት አመላካች ነው።

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ገበያውን ለማረጋጋት በማሰብ በመጋቢት ወር ከአባላቱ የአደጋ ጊዜ ክምችት 400 ሚሊዮን በርሜል ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 164 ሚሊዮን በርሜል ያህሉ እስካሁን ጥቅም ላይ ውሏል። በሚያዝያ ወር የአደጋ ጊዜ ክምችት አቅርቦት ፍጥነቱ መጨመሩን እና በቀጣዮቹ ወራት ተጨማሪ የነዳጅ ምርት ወደ ገበያ እንደሚገባም ኤጀንሲው አክሎ ገልጿል።

በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የክረምት (የበጋ) የጉዞ ወቅት እየተቃረበ በመምጣቱ፣ የነዳጅ እጥረት ስጋት ይበልጥ እያደገ መጥቷል። የአቅርቦት መስተጓጎሉ የሚቀጥል ከሆነ በአጭር ሳምንታት ውስጥ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አየር መንገዶች አስቀድመው እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። ከፍተኛ የክረምት የነዳጅ ፍላጎት ወቅት ከመምጣቱ በፊት የዓለም የነዳጅ ክምችት በፍጥነት እየተመናመነ መምጣቱ፣ በቀጣይ በዋጋው ላይ ከፍተኛ መዋዠቅ ሊፈጥር እንደሚችል ታምኖበታል።

በሌላ በኩል ይህ እያሻቀበ የመጣው የነዳጅ ዋጋ እንደ ፔትሮኬሚካል እና ከባድ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉ ተጠቃሚዎች ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ እያስገደዳቸው በመሆኑ፣ በአጠቃላይ የነዳጅ ፍላጎት ላይ ጫና ፈጥሯል።

ከጦርነቱ መፈንዳት በፊት በሁለተኛው ሩብ ዓመት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ፍላጎት በቀን 3.5 ሚሊዮን በርሜል ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን በቀን በ2.4 ሚሊዮን በርሜል ብቻ ሊቀንስ እንደሚችል አይ.ኢ.ኤ አዲሱን ግምቱን አስቀምጧል። በአንጻሩ የነዳጅ ላኪ ሀገራት ድርጅት (OPEC) በበኩሉ፣ እ.ኤ.አ በ2026 የዓለም የነዳጅ ፍላጎት በቀን በ1.2 ሚሊዮን በርሜል ያድጋል የሚል ጠንካራ እምነት እንዳለው አስታውቋል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.