Logo
YenetaTube
ኢራን ወዲያውኑ የሆርሙዝ ወሽመጥን ከፍታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ካልመጣች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሲኦል ይወርድባታል- ትራምፕ

የኔታ ሚዲያ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ እጅግ ጠንካራና አስደንጋጭ የተባለ ማስጠንቀቂያ ሰጡ። ፕሬዝዳንቱ በዛሬው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት ኢራን በቁጥጥሯ ስር የሚገኘውን የሆርሙዝ ወሽመጥ በአስቸኳይ ካልከፈተችና የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድባት አስታውቀዋል።

ይህ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ፍጥጫ የተቀሰቀሰው የኢራን ጦር በስትራቴጂካዊው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሲበር የነበረን የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን (A-10 Thunderbolt II) መትቶ መጣሉን ተከትሎ ነው።

ኢራን አውሮፕላኑ የአየር ክልሌን ጥሷል የሚል ክስ ብታቀርብም ዋሽንግተን ግን ድርጊቱን ቀጥተኛ የጦርነት ትንኮሳ በማለት ፈርጅታለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢራን ወዲያውኑ ወሽመጡን ከፍታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ካልመጣች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሲኦል ይወርድባታል (All hell will reign down)" በማለት አስጠንቅቀዋል።

ይህም ፕሬዝዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለኢራን የሰጡት እጅግ የመጨረሻውና ጠንካራው ማስጠንቀቂያ ሆኖ ተመዝግቧል።

የአለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚሸጋገርበት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት በአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ተሰግቷል።

የአሜሪካ አምስተኛው የባህር ኃይል ክፍለ ጦር እና በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በከፍተኛ ጥንቃቄ ላይ እንዲሆኑ ትዕዛዝ ተላልፏል።

በበኩሏ ኢራን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗንና የአሜሪካ የኃይል እርምጃ ቀጠናውን ወደማይወጣበት ቀውስ እንደሚከተው ገልጻለች።

እንደ ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ያሉ የአሜሪካ አጋሮች ውጥረቱ ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳያመራ ለማርገብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንት ትራምፕ የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ መጪው ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2026 የሚያበቃ በመሆኑ አለም ቀጣዮቹን ሰዓታት በከፍተኛ ስጋት እየተጠባበቀች ትገኛለች።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.