Logo
FastMereja
የ8 ዓመታት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ፦ ከጥገኝነት ወደ ዘመናዊና ዘርፈ-ብዙ እድገት አሸጋግረናል ተባለ
#fastmereja I የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡ የኢኮኖሚ ለውጦችን የሚገመግም መግለጫ አውጥቷል። በዚህም ሀገሪቱ ቀደም ሲል ከነበረችበት የውጭ ብድር ጥገኝነት እና ጠባብ የንግድ አማራጮች በመውጣት፣ በገበያ መር ሥርዓት የሚመራና በዘርፈ-ብዙ መስኮች ላይ የተመሰረተ መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገች መሆኑ ተመልክቷል። በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት ማምጣት የጀመሩ ሲሆን፣ በተለይም የግብርናው ዘርፍ በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ እንደ ትልቅ ስኬት ተጠቅሷል። በ2017 ዓ.ም ብቻ ከስንዴ ምርት 2.65 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም በ"አረንጓዴ አሻራ" መርሃ ግብር 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውና የደን ሽፋኑ ወደ 23 በመቶ ማደጉ ለኢኮኖሚው ዘላቂነት መሠረት መጣሉ ተገልጿል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ "ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች" (Special Economic Zones) መቋቋማቸው እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በምርት ሂደት ላይ ያላቸው ድርሻ ወደ 65 በመቶ ማደጉ የመዋቅራዊ ሽግግሩ አካል ተደርጎ ተወስዷል። በማዕድን ዘርፍም በተለይም የወርቅ ምርት በ2017 ዓ.ም 3.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። የዲጂታል ኢኮኖሚውን በሚመለከት የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 87.9 ሚሊዮን መድረሱ እና የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ የፋይናንስ ተደራሽነትን እንዳሳደገው ሪፖርቱ ያሳያል።

በከተማ ልማት ረገድ "የኮሪደር ልማት" ስራዎች በአዲስ አበባ እና በ56 ከተሞች መተግበራቸው ከተሞችን ለኑሮና ለስራ ምቹ ከማድረጉም በላይ፣ የሀገሪቱን ገጽታ በመቀየር ለቱሪዝም እና ለንግድ እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። መንግስት ይህን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ በመቀጠል፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት መተለሙን በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ሰፍሯል።

መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.