Logo
Getu Temesgen
👉የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚያስመሠግን ስራ በቢሾፍቱ

♦️የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች የት ነው ያሉት?
#ethiopia | የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ቢሾፍቱ መሽገዋል፤አንድ ሠው መቅረት የለበትም የተባለ ይመስል ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያልን ጨምሮ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ማለትም ከቲቪ፣ከሬዲዮ፣ከፕሬስ፣ከፎቶግራፍ፣ከቲክታክና ከአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች የቱሪስት ከተማ በሆነችው ቢሾፍቱ በሚገኘውና በአዲስ መልክ ደረጃውን ጠብቆ በተሠራው ሌክ ቪው ሆቴል ተጠቃለው ገብተዋል።

♦️ቢሾፍቱ ሌክ ቪው ሆቴል የመግባታቸውስ ምስጢር ምንድነው?

የዚህ ምክንያታቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለስፖርት ጋዜጠኞች ባዘጋጀው የሁለት ቀናት(መጋቢት 17-18) የስልጠናና የምክክር መርሃ ግብር ላይ ለመገኘት ነው።

♦️የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ስልጠናና የምክክር መድረክ ምን ምን ያካተተ ነው?

በቢሾፍቱ ሌክ ቪው ሆቴል በተዘጋጀው የሁለት ቀናት የስልጠናና የምክክር መድረክ በተመረጡ አራት ርዕሶች ዙሪያ ትምህርት ይሠጣል፤እነሱም የኦሎምፒክ መርሆች፣ የኦሎምፒክ እንቅስቃሴ እሴቶችና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች፣የኦሎምፒክ ቻርተርና ዋና ዋና ይዘቶች፣የስፖርት ጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን እንዲሁም መንግስትና ስፖርት በሚሉ በውስጣቸው ሠፊ ጉዳዮችን በያዙ ርዕሶች ላይ ስልጠናና ምክክሮች ይካሄዳሉ።

♦️ስልጠናውን የሚሠጡት ባለሙያዎች(ምሁራን) እነማን ናቸው?

ስልጠናው እየተሠጠ ያለው ከፍተኛ ልምድን ከዕውቀት ጋር ባጣመሩ ባለሙያዎች(ምሁራን)፣ስፖርቱ በከፍተኛ ኃላፊነት በመሩ ኢንስትራክተሮች ሲሆን እነሱም ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተርና የኮተቤ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ ሙሉነህ ግርማ፣ከ39 ዓመታት በላይ ስፖርቱን ባገለገለው፣የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፅ/ቤት ኃላፊ፣የኢትዮጵያ የስፖርት ሳይንስ ማህበር መስራችና ፕሬዝዳንት፣የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቴክኒክና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ቢልልኝ መቆያ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር(ሌክቸረር)ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ናቸው።

♦️መድረኩን በይፋ የከፈቱት አቶ ሚኒልክ ሐብቴ "ጋዜጠኞች መልቲ ዳይሜንሽናል ናቸው"

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀውን የምክክር መድረክ በይፋ መጀመሩን በንግግራቸው ያበሠሩት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ አባልና የኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሚኒልክ ሐብቱ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸውም
"ጋዜጠኞች መልቲ ዳይሜንሽናል ናቸው ተብጨሎ ይታሠባል፤ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ ነው እንደ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣እንደ ፌዴሬሽኖች ያላየናቸውን የሚሳዩን መስታዎቶች ናቸውና ከእናንተ ጋር ይሄንን የምክክር መድረክ በማዘጋጀታችን ከእናንተ የምንማርበት፣ከእኛም ከኢንስትራክተሮቻችን የምትማሩበት መድረክ ይናል።በድጋሚ ወደ መማማሪያና የምክክር መድረክ መጣችሁ" ብለዋል።

♦️ስልጠናውና የምክክር መድረኩ ዛሬ በልዩ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ይጠናቀቃል
ከቲቪ፣ከሬዲዮ፣ከፕሬስ፣ከፎቶግራፍ፣ከቲክታክና ከአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ከ60 በላይ አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች ባልተለመደ መልኩ በብዛትና በንቃት የተሳተፉበት የስልጠናና የምክክር መድረክ ዛሬ በልዩ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት የሚጠናቀቅ ይሆናል።

በባለሙያዎች ከተሠጠው ትምህርት በተጨማሪ የስልጠናው ተካፋዮች በ4 ምድብ ተከፍለው ውይይት ያደረጉ ሲሆን አጋጣሚው የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማድረጉም በላይ የተራራቁና የማይቀራረቡ የሚዲያ ባለሙያዎች ይበልጥ ተቀራርበው የሚሠሩበት፣የሚመካከሩበት፣መልካም ግንኙነት የፈጠረ መልካም አጋጣሚም ሆኖ ተገኝቷል።የስልጠናና ምክክር መድረኩ ዛሬ ሲጠናቀቅ ለተሳታፊዎች ሠርተፊኬት የሚሠጥ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለጋዜጠኞች ክብር የእራት ግብዣም መዘጋጀቱ ነው የተሠማው።

♦️በመጨረሻም ምስጋና

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊነቱን ወስዶ ለጋዜጠኛውና ለሙያው አስቦ ይሄን መሠል ውጤታማ የስልጠናና የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ ፕሬዝዳንቱን ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስንና የስራ አመራር ቦርዱን በአጠቃላይ ያስመሠግናቸዋል።በሁለት ቀን ስልጠና ብቻ ክፍተቱን ለመሙላት ስለማይቻል ተከታታይነት ባለው መልኩ ቢቀጥል ዘርፉ የበለጠ እንዲሻሻል ብቻ ሳይሆን ይበልጥ በዕውቀት እንዲሠራ ይረዳልና በደንብ ቢታሠብበት የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፤ስልጠናው አስልቺ ከመሆን ይልቅ የጋዜጠኛውን ስሜትና ፍላጎት ባማከለ መልኩ ያሳለጡት ዋና አጋፋሪ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ስልጠናውን የሠጡት ባለሙያዎችን በመጨረሻም በቢሾፍቱ የነበረን የሁለት ቀናት ቆይታ ምቹና ያማረ እንዲሆን እንዲሁም ለጋዜጠኞች ክብር የእራት ግብዣ ያደረጉትን ደረጃውን የጠበቀው ምቹና ዘመናዊው የሌክ ቪው ሆቴል ባለቤቶችን የዜና ሠዎች በመጨረሻም አመስግነዋል።

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.