Logo
FIDEL POST NEWS
በዓለም ላይ ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር እንዴት አዎንታዊ መሆን ይቻላል?

​"ቀውሶችን ለማሸነፍ የአስተሳሰብ መንገዳችንን መለወጥ አለብን።"

ከሲዊዘርላንዳዊቷ ፀሀፊ ሳንድራ ማርሽነር ፅሁፍ የተወሰደ

​በየቀኑ በአዳዲስ ዜናዎች እንጋፈጣለን - በጦርነት ቀጠናዎች ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሞቶች፣ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ግጭቶች ወይም ቀውሶች። ታዲያ ይህን ውጥረት የነገሰበትን የዓለም ሁኔታ እንዴት ልቋቋመው ይገባል?

​በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንድ ሳምንት ሆኖታል፤ በዩክሬን ያለው ጦርነት ለአራት ዓመታት ሲያስጨንቀን ቆይቷል፤ ብቻ አለም ላይ እዚህም እዛም ጦርነትን ግጭት አለ።

ዓለም ከመስመሯ የወጣች ትመስላለች። በየቀኑ ከመላው ዓለም በሚመጡ ዜናዎች እንደበድባለን - አንዱ ከሌላው የከፋ አሉታዊ ዜና። እነዚህ ሁሉ ቀውሶች በውስጣችን ምን ይፈጥራሉ? ተስፋንስ እንዴት ማግኘት እንችላለን?

​ይህ ጥያቄ "Confidence" (መተማመን) በሚለው በቅርቡ ባሳተመችው መጽሐፏ ሉዊዝ ብራውን የተባለች ጀርመናዊ-እንግሊዛዊ ደራሲ ዳስሳዋለች።

ጦርነቶችና ቀውሶች በብራውን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። በመሆኑም በሕይወቷ ውስጥ የበለጠ መተማመንን ለማምጣት ልዩ ዘዴ ለመጠቀም ወሰነች።

በራሷ ላይ ስላደረገችው ሙከራም "ደር ቡንድ" ለተባለው የዕለታዊ ጋዜጣ ገልጻለች።

​አስደሳች ገጠመኞችን በየቀኑ መመዝገብ

​ለአንድ ዓመት ያህል፣ ብራውን በዕለት ተዕለት ሕይወቷ ውስጥ ያጋጠሟትን አዎንታዊ እና ቆንጆ ነገሮች ሁሉ ጻፈች። እነዚህ በጣም ጥቃቅን ጊዜያት ሊሆኑ ይችላሉ - ለምሳሌ በፀሐይ ብርሃን የሚያንጸባርቅ የቤት ግድግዳ ወይም እንደ ዳንስ የሚንቀሳቀሱ የግንባታ ክሬኖች።

​"አንድ አዎንታዊ ነገር በጻፍኩ ቁጥር በውስጤ መጠነኛ መነቃቃት እንደሚሰማኝ ወዲያውኑ ተረዳሁ። ልክ ትንሽ የወርቅ ቁራጭ በኪሴ ውስጥ እንዳስቀመጥኩ ያህል ነበር" ትላለች። ይህ ደግሞ ብዙ ቆንጆ ተሞክሮዎችን እንድትጽፍና በንቃት እንድታጣጥማቸው አበረታቷታል።

​ሁኔታውን ለመቋቋም የሚረዱ 3 ዋና ምክሮች

​1. መካከለኛውን መንገድ መፈለግ

​አንዳንዶች ራሳቸውን ከዓለም አቀፍ ቀውሶችና ዜናዎች ሙሉ በሙሉ ሲያግሉ፣ ሌሎች ደግሞ የቅርብ ጊዜ ዘገባዎችን ለማግኘት በየሰዓቱ ስልካቸው ላይ ይቆያሉ። ሁለቱም ጽንፎች ችግር እንዳላቸው የስነ-ልቦና ባለሙያዋ ኢቪክ አድለር ያስረዳሉ። ራስን ማግለል ወደ እውነታው መሸሽ ሲያመራ፣ ከመጠን በላይ መረጃ ደግሞ የአእምሮ ሰላምን ይነሳል።

​መፍትሄው፦ ስለ ዓለም ክስተቶች መረጃ ይኑርዎት - ነገር ግን በመጠኑ። አእምሯችን በቀን ውስጥ ሊቀበለውና ሊያቀነባብረው የሚችለው የመረጃ መጠን ገደብ ስላለው ለስማርትፎን አጠቃቀም የተወሰነ ጊዜ መድቡ።

​2. ሚዛንን መፍጠር

​ከቀውሶች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጫና በንቃት መመከት ይቻላል። ለፕሮጀክቶች መዋጮ ማድረግ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እና በጎ ፈቃደኝነት ይመከራሉ።

የስነ-ልቦና ባለሙያዋ ማይሪየም ቶማ እንደሚሉት፣ የማያቋርጥ የዜና መዓት "ሥር የሰደደ ውጥረት" ይፈጥራል። ይህ ውጥረት በአካልም ጭምር (የራስ ምታት፣ የጡንቻ መኮማተር) ሊገለጽ ይችላል።

​መፍትሄው፦ በሜዳ ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከተፈጥሮ ጋር መገናኘት እና እውነተኛ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር። አእምሯችን "የአደጋ ደወል" ከመደወሉ በፊት የሰውነታችንን ድምጽ መስማት መማር አለብን።

​3. የአስተሳሰብ ዘይቤን መለወጥ

​ቀውሶችና ጭንቀቶች ባዮሎጂያዊ ውጥረት (stress) ያስከትላሉ። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ለአእምሮ ህመም የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።

​መፍትሄው፦ "ቀውሶችን ለመቆጣጠር የአስተሳሰብ ዘይቤያችንን መቀየር አለብን" ይላሉ የነርቭ ሳይንቲስት ማረን ኡርነር። ከአይን አውጣ አስተሳሰብ ይልቅ ወደ ተለዋዋጭ እና መፍትሄ ተኮር አስተሳሰብ መሸጋገር ያስፈልጋል።
"ለምን?" ከማለት ይልቅ "ለምን ዓላማ? (ለምን ይበጃል?)" ብሎ መጠየቅ የተሻለ ነው።

​በተጨማሪም የመርዳት አቅም እንደሌላችሁ ከተሰማችሁ የሚከተሉትን ዝርዝሮች መጻፍ ትችላላችሁ፦ "ለእኔ አስፈላጊው ነገር ምንድን ነው? በሕይወቴ ወዴት መሄድ እፈልጋለሁ?" ይህ በራስ የመተማመን እና ነገሮችን የመለወጥ አቅም እንዳላችሁ እንዲሰማችሁ ያደርጋል።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.